አፈር ስሆን አልበም እንዳትጋብዢኝ
አፈር ስሆን አልበም እንዳትጋብዢኝ
በግሩም ተ/ይማኖት
እዚህ አረብ ሀገር ያሉ እህቶቼ ፎቶ በፎቶ ናቸው፡፡ ወደ ሀገር ቤት
ከብር/ዶላር/ ይልቅ የሚልኩት ፎቶ በመብዛቱ በአንድ ወቅት ‹‹የጫዎታ ኩኪስ›› የሚል ቀልድ ያቀረበ አንድ ኮሚዲያን በቀልዱ ላይ
‹‹…ልጄ ፎቶ ላከች..›› ሲሉ አንደኛዋ ሴትዮ ሁለተኛዋ ‹‹..ሁሉም የሚልኩት ፎቶ ነው፡፡ እስኪ አስቀምጪው ድንገት ስትመጣ ትዘረዝረው
ይሆናል…›› የሚል ቃላት አካቶበታል፡፡ እውነታነት አለው፡፡ እዚህ የመን ያለ ኢትዮጵያዊ በየቤቱ፣ በየቦርሳው የማየው የፎቶ አልበም
ብዛት ምነው ብሩን እንዲህ ቢይዙት፣ ቢያስቀምጡት ያሰኛል፡፡ ከአቅም በላይ ወጪ በማውጣት በፉክክር ሰርግ መደገስ የተለመደ
ነገር ሆኗል፡፡ ታዲያ ቀሪው ቪዲዮ ነው፣ ፎቶ ነው፡፡ እግር ጥሎዎት፣ ጥሪ ጎትቶት፣ እክል ገጥሟቸው ለመጠየቅ ቤታቸው ጎራ ካሉ
ፈረደቦት፡፡ የአይንዎ ብሌን ተጎልጉሎ እስኪወጣ የፎቶ ክምር ይቀርብሎታል፤ አይንዎ እንኪጠናገር የሚያዩት ቪዲዮ ይከፈትሎታል፡፡
ታዲያ ምን ቸገረኝ መኮምኮም ነው ካሉ የራስዎ ጉዳይ ራስዎ ይወጡት፡፡
እኔ ግን ስልችት ብሎኛል፡፡ ከሁሉ ከሁሉ ግን የሰለቸኝ ፎቶውን ተከትሎ የሚንጋጋ ቆርፋዳ ወሬ ነው፡፡ አንድ ወዳጄ እና ሚስቱ ከሁለት
አመት በላይ ሰርተው ያጠራቀሙትን ገንዘብ አራግፈው ሰርግ ደገሱ፡፡ ሰርጉ ላይ እኔም ነበርኩ ታድሜያለሁ፡፡ ያውም ፕሮቶኮል
ነገር ልጠብቅ ብዬ የማልወደውን ሱፍ ሱሪና ኮት ለብሼ እንደ አቅሜ ትከሻዬን ሰብቄያለሁ ምንም እንኳን ወባ የያዘው ብመስልም፡፡
ሰርጉ ባለፈ ሳምንት ስልኬን ከስልኩ የተወረወረ ጥሪ ኮረኮረውና አንቃጨለ፡፡ የመጣውን ድምጽ እንዲያመጣ OK የሚለው ላይ ደነቆልኩት፡፡
‹‹ሀሎ!..›› አለኝ ከወዲያ ማዶ፡፡
‹‹ዛሬ ከሰዓት በኋላ ቤት ነን ና..›› አለኝ እና ከምሰራበት ስወጣ ቤታቸው
እንድገኝ ጋበዘኝ፡፡ እዚህ ሀገር ጥሪ ሲኖር ባዶ እጅ አይኬድም ጫት ጠልጠል ይደረጋል፡፡ ግዴታ ባይሆንም እነሱ እያኘኩ
በሚያወሩት የምርቃና ወሬ ላለመደንዘዝ ፍቱን መድሀኒት ነው፡፡ ታዲያ ምሳ ከራስህ፣ ጫት ከራስህ፣ ውሀ ከራስህ፣ ሲጋራ ከራስህ፣
የምትፈልገውን ሁሉ ከራስህ…መቀመጫ ከእነሱ ቡና ያጠጡሀል፡፡ ለነገሩ ቡናውንስ ማን አየው? ቡናም የሌለበት… እየቃምክ ተፋጠጥ፣
ቀደዳ ቅደድ አይነት ሴሪሞኒ ያለበትም ቦታ አለ፡፡ ሺሻ አጫሽ ከሆንክ ወረፋህን እየጠበክ ማቡነን ነው፡፡
እና እላችሁ መቼም ጠሪ አክባሪ ነው ብዬ ጫት አንጠልጥዬ
እብስ…የሰርጋቸው እለት የተቀረጸው ቪዲዮ እየታየ ነው፡፡ ሙሽራው ደረቱን ነፍቶ አቀማመጡ ማን እንደ እኔ የሚል ይመስላል፡፡ የሰርጉ
እለት ፍርሃት ይሁን ድንጋጤ ዝናብ የመታው ውሻ መስሎ ነበር፡፡ አሁን በሀብታሚኛ ነው የተቀመጠው፡፡ ‹‹ኦ!..የእናቴ ልጅ..እንኳን ደህና መጣህ..የሰርጉን ቪዲዮ እያየን
ነው፡፡..›› በማለት ጀመረና በቀጣይ ዙሮች የጉራ ቀደዳው ‹‹…እይ የእኔ ሰርግ እዚህ ሀገር ተስተካካይ የለውም፡፡ ከእነ
እከሌ..ከእነ እከሌ ይበልጣል፡፡..ደግሞ እንደማንም ተበድሬ እንዳይመስልህ የደገስኩት፡፡…›› አባባሉ አናደደኝ፡፡ ባዶ ነገር
ያዘለ ስሜት ተሰማኝ፡፡ አቅምን ያላገናዘበ ድግሳቸው አቅምን ላላገናዘበ ጉራቸው ሲባል መሆኑ ታወቀኝ፡፡ በዛ ላይ ወደ ሁለት
ሺህ ዶላር ብድር ገብቶ መደገሱን እያወቅን ለጉራ መዋሸቱ አናዶኛል፡፡ ቢሆንም ፊልሙን እያየሁ ነው፡፡ ንዴቴ በውስጤ ነው
እንዴት ትንፍሽ ልበል? ይሉኝታ የሚባል ገመድ ጠፍሮኝ፡፡ …የሲዲውን ብዛት ተዉኝ፡፡ ከጠዋት ጀምሮ ማታ እስኪተኙ ነው
የተቀረጸው መሰለኝ፡፡ ተኝተው የሰሩትንም ቀርጸው አለማቅረባቸው ተመስገን አሰኘኝ፡፡
የዛን ጊዜ የተጀመረው ፊልም እዛ ቤት በሄድኩ ቁጥር ሁሌ እሱ ነው፡፡ ሁሌ
እሱ ነው…እንኳን እኔ የቤቱ DVD አስሬ ከሚከፍቱ ከሚዘጉኝ ብሎ በቃሉ አጥንቶ ይዞታል፡፡ ያለ ሲዲ ገና ፓዎር ሲበራ መስራት
ይጀምራል፡፡ ሌላ ሲዲ እንደማይገባ አውቆታል፡፡ ሰለቸኝ፡፡ ስልችት ማለት ብቻ ሳይሆን ቅልሽልሽ እስኪለኝ ከሰባት ጊዜ በላይ
አየሁት፡፡ በዛ ላይ ማየት ብቻ ቢሆን እኮ ጥሩ ነው፡፡ ይሄ እከሌ ነው ይሄ እየጨፈሩ ነው…የምናየውን ደግሞ ሲነግረን እያየን ነው
እስኪ እንይበት ብንል ማን ሊሰማን፡፡ ሌላ ወሬ ከያዝን ፖዝ አድርጎ እዩት እንዳያልፋችሁ ይላል፡፡ ሰው እስኪሰለች እዩልኝን
ምን አመጣው?… አሁን ፊልሙን ሽሽት እዛ ቤት እርግፍ፡፡
ሌላው
ደግሞ እጅግ አድርጎ የሚገርመኝ ኢትዮጵያ ፍቅረኛ አላት ወይም አለው ለመባል እዚህ የሚያደርጉት ነገር ነው፡፡ አንዷ ጎረቤቴ
የነበረች ልጅ በምንም መንገድም ሆነ በስህተት ስለ ፍቅረኞችም ሆነ ስለ ወንድና ሴት ከተወራ ትጀምራለች፡፡ ‹‹ውይ እኔ እና ተስፍሽ…››
በማለት ትንደረደርና…ማቆሚያ የሌለው የፍቅር ገድል ይተረካል፡፡ ታዲያ መደምደሚያው የመን ስለጠበሰችው ነው፡፡ የሚገርመው ግን ስለፍቅር እያወሩ ስትመጣ ‹‹መጣች በሉ አቁሙ ሌላ አውሩ..›› የሚሏት
ሁሉ አሉ፡፡
ከጀመረች ‹‹ ተስፍሽ ቦይ ፍሬንዴ….›› የመጀመሪያ መግቢያዋ ነው፡፡
ትንሽ ቆይቶ ቦርሳዋ ይከፈታል ፎቶ ይወጣል፡፡ ያለ ማጋነን ከ50 ጊዜ በላይ ‹‹ቆንጆ›› አይደል? የሚል ጥያቄ ታክሎበት
አሳይታኛለች፡፡ ቁንጅናውን እንዳደንቅ ተገድጃለሁ፡፡ ለእኔ ቁንጅናው ያለው ሰው መሆኑ ላይ ነው፡፡ ከእሱ ጋር ስለተዝናኑበት
ሆቴል እና መናፈሻ ሁሉ ሲወራልኝ ጆሮዮ እስኪደንዝ ሰምቻለሁ፡፡ ከመስማቴ ብዛት ሚሞሪዮ ሴቭ አድርጎት ገና እሷን ሳይ
ያንቃጭልብኛል፣ ያንሾካሹክልኛል፡፡ በመጨረሻ ግን ከእለታት አንድ ጎዶሎ ቀን እኛን እንደ ደቡብ አፍሪካ ከወሬ አፓርታይድ ነጻ
የሚያወጣን አጋጣሚ ተከሰተ፡፡ የሰፈሯ ልጅ በእንግድነት መጣችና ፎቶው የአጎቷ ልጅ እንጂ ፍቅረኛዋ አለመሆኑን ፊት ለፊቷ
ባለማወቅ በስህተት አጋለጠቻት፡፡ እፎፎፎይ!...ተገላገልን፡፡ ከዛን ጊዜ በኋላ ተሳስታ እጇን ወደ ቦርሳዋ ስትሰድ ‹‹አፈር
ስሆን አልበም እንዳትጋብዢኝ እያልኩ አበሽቃት ጀመር፡፡
ስደት ለውሽት ያመቻል እያሉ ስንቱን ሰማን እባካችሁ፡፡ ኢትዮጵያ
እያሉ ፍቅረኛ መያዝ ከአራዳ ልጅ ሊያስቆጥር ነው ወይስ ትሪፐኛ ሊያሰኝ? አንዴ ደግሞ ቅድስት የምትባል ልጅ የገጠማትን
ላውጋችሁ፡፡ ኢትዮጵያ እያለች በጣም ቀጭን ነች፡፡ ከቅጥነቷ የተነሳ እንደ ምላጭ ከጎን አትታይም፡፡ ሳሪስ ንፋስ ስልክ ነው
የተማረችው፡፡ ወደ የመን ከመጣች 10 አመት አስቆጥራለች፡፡ የአባቷን መሞት ተረዳችና ልናስተዛዝን ሄድን፡፡ ለቅሶ ላይ ሀዘን
ማስረሻ ጫዎታ ይደራል፡፡ ጫት ይታኘካል፣ ቡጨቃ ይቦጨቃል፣ ምግብ ይበላል፣ ቆሎ እየተቆረጠመ ቀደዳው ይቀደዳል፡፡ ተረኛ
ነኝና…የሚለውን አቀንቅኖ መሀሙድ ኢትዮጵያ ስለነበረች ፍቅረኛው ወሬ ጀመረ፡፡ ታሪኩን ሲተርከው ጥሩ የህንድ የፍቅር ፊልም
የሚሰሩ ሁሉ አስመስሎታል፡፡ አንቦ ኢትዮጵያ ሆቴል ስላሳለፉት ደስታ እና ዋና…ሲያወራ ውሸቱን ለማወቅ ጊዜ አልጠየቀብኝም፡፡
‹‹አንቦ ስንሄድ ሱሉልታ ላይ…›› ሲል አንቦን እንደማያውቀው እየታዘብኩ መሀንዲስ ሳያስፈልገው በሱሉልታ መንገድ ሲቀይስለት
ጉዳይ ስለነበረኝ ጥዬ ወጣሁ፡፡ እዛው የቆዩ ልጆች ግን መጨረሻውን ሲነግሩኝ እንኳን በሰዓቱ አልነበርኩ ለእሱ እኔ አፍር ነበር
ነው ያልኩት፡፡
ስለፍቅር ህይወቱ የተቀነባበረ ፈጠራውን ሲነዛባቸው ቆይቶ የኪስ
ቦርሳውን መዥረጥ አድርጎ የፍቅረኛውን ፎቶ እዩልኝ በሞቴ አይነት ግብዣውን ያቀርባል፡፡ እየተቀባበሉ ማየት ጀምረው ቅድስቴ እጅ
ፎቶው ደረሰ፡፡ ያ-ሁሉ ታሪክ የተወራላት ፍቅረኛ የተባለችው ልጅ ፎቶ የቅድስት ዘጠነኛ ክፍል እያለች ከጓደኞቿ ጋር የተነሳችው
ከለር ፎቶ ነው፡፡ ያኔ ቀጭን በመሆኗ አሁን ከመጠን በላይ በመወፈሯ መሀል ነው ለውጡ፡፡
‹‹አንተ ይሄማ የራሴ ፎቶ ነው ካንተ ጋር የት ተዋውቀን ነው ፍቅረኛህ
የሆንኩት?...›› አስቡት ቤቱ ሁሉ ጸጥ ብሎ ሲሰማ፡፡ ‹‹..ያንቺማ አይደለም..›› ብሎ ሲደርቅ ያዛኑ ፎቶ ኮፒ ከሻንጣዋ
አውጥታ ለሰዉ ሁሉ አሳየች አሉኝ፡፡ በእፍረት አንገቱን ሲደፋ አስቤ ወዲያው የብስራት ጋረደው ዘፈን ነው የታወሰኝ ‹‹እኔ
አንገቴን ልድፋ ላቀርቅርልሽ..›› የሚለው፡፡ ብቻ ምን አለፋችሁ አሁን አሁን ስለፎቶ እያወሩ ወይ ስለፍቅረኛ እየተወራ ሴቶቹ
እጃቸውን ወደ ቦርሳቸው ከላኩ ‹‹አፈር ስሆን አልበም እንዳትጋብዢኝ..›› የምትለውን በውስጤ አንጎዳጉዳለሁ፡፡ አፍ አውጥቼማ
እንዳልናገር ይሉኝታ…ፌስቡክ ላይ ይሉኝታ ሜድ ኢን ኢትዮጵያ የሚል ጽሁፍ አይቼ ነበር፡፡ ካገኛችሁት ትክክል ብላችሁ
አስምሩበት፡፡ የፎቶው ጉዳይ ወንዶቹም የኪስ ቦርሳቸውን ሲመዙ ‹‹..አፈር ስሆን የተመረጠች የቆንጆ ልጅ ፎቶ ፍቅረኛዬ ነበረች
ብለህ እንዳትጋብዘኝ..›› እላለሁ፡፡ ቆይ አረ ሁሉ
የቆንጆ..ቆንጆዎችን..ፎቶ እየያዘ ፍቅረኛ ካደረገ ቆንጆ ያልሆነ አይወደድም ያለው ማነው? እንዴ እኛንስ ማን ሊወደን ነው?
በመጨረሻም የፎቶ አልበም አለዎት? የት ያስቀምጡታል? ለሰዎች
በየትኛው ወቅት ይጋብዛሉ? እነዚህን ጥያቄዎች ያቀረብኩት ያለነገር አይደለም፡፡ እባክዎ ሰው ባልፈለገበት እና በየቦታው አልበም
እያወጡ አያሰልቹ ለማለት ነው፡፡
በሌላ ትዝብት እስክመለስ ጨረስኩ ሰላም እንሰንብት
0 Comments:
Post a Comment
Subscribe to Post Comments [Atom]
<< Home