Monday, October 1, 2012

ይሄን ግን ባታነቡት ይሻላል


ይሄን ግን ባታነቡት ይሻላል

ምንም የማይረባ ነገር ልንገርህ /ልንገርሽ/
              በግሩም ተ/ሀይማኖት
    ሁሉ አማረሽን ገበያ አታውጧት ይላሉ እማማ ሊሊ…እህ ሁሌ ለማሾፍ ሲባል፣ በተተረተ ቁጥር አስካለ፣ ማሚቴ…ማሞ ምናምን እያልን እንኑር እንዴ እነሱዚ፣ ሶፊ፣ ኪኪ፣ ሳሚ.. አይተርቱም? አያረጁም ያለው ማነው? ወጣት የነብር ጣት እንደሚሉት ነህ እንበል፡፡ እንበል እንጂ ባትሆንም እንኳን እንደወጣት አስበህ ቦርሳህን ስበህ ያለህን ባውንድ እየመዠረጥክ ልጅህን ልጅህን የሚያክሉ ህፃንትን ትገዛና ተጋድመህ ታጋድማቸዋለህ፡፡ በቃ! ተጋድመህ ምን ልትሰራ ማለት ይከብዳል፡፡ መቼም ቤርጎ ተከራይተህ ለጸሎት ነው አይባልም፡፡ እንዲህ አይነት አመል ያላችሁ ሰዎች ግን ይሄን ባታነቡት ይሻላል፡፡ ደም ብዛታችሁ ተነስቶ፣ተንተክትኮ…ስኳራችሁ ወደ ጨውነት ተቀይሮ እንዳታማርሩኝ፡፡ ግን የምናገረው እውነት ነው፡፡   

   ምንም እንኳን በጉብዝናህ ወቅት እግዚአብሄርን አስቡ ቢልም ነገር አንሸዋረን ስናረጅ ነው የምናስበው፡፡አንተም እንደዛ ብታስብ እድሜህ ፊትህን ወደ እግዚአብሄር ቤት ማዞሪያው ላይ ይሆናል፡፡ ያንንም አልፈህ ‹‹ሩጫዬን ጨርሻለሁ..›› ቅበሩኝ ላይ ደርሰህ ቢሆንም ብር እንደ ወጣት አሳስቦህም ይሆናል፡፡ ለነብስህ ቤትክርስቲያን ለስሜትህ ቤርጎ እየተመላለስክም ደጅ ትጠናለህ…ግን አትድንም፡፡ በዝሙት የመጣውን መቅሰፍትም አስብ፡፡ አትዘሙት እንጂ በርትተህ ሰው ቆፍር አይልም ቃሉ፡፡ በትረ ሰለሞንህን አሽመልምለህ ጦዘህ ጥንቅሽዋን ታጦዛታለህ እቤት ግን ሚስትህ አንተን በሀሳብ እየሳለች ትራስ ታቅፋ ትዝታ ሆኖባት ነገሩ ጣቶችዋን ከስሜት ጋር እያፋተገች ስራ አብዝታባቸው ቢሆን ይፈረድባታል፡፡ ይህ እውነት ነው፡፡ የምናወራው ሁሉ እውነት ነው፡፡ መደባበቅ ይብቃ፡፡

    ሹገር ዳዲ ተብለህ ሽበትህን አቅልመህ ኪስህን መዋረጃ አርገህ ጋልበህ አስጋልበህ ስትገባ ቤት ያለችው ጌጥህን ታቆሽሻታለህ፡፡ የተራረፈ ውጥረታዊ ገላህን ይዘህ ከአቅም በታች በመጫዎት በነካ የተባለ ይመስል አትክልት ውሀ እንደሚያጠጣ ቀድመህ ትደፋና ማንኮራፋትህን በትላክተሪኛ ታስነካዋለህ፡፡ በአለቀ ጉልበት /ፊያቶ/ ገብተህ ተልሞስሙሰህ ታልሞሰሙሳታለህ፡፡ …ኤጭ! እየበረርክ ሄደህ ፍሬን ሳትይዝ ዘለህ የወረድክበት መኪና ሄዶ ሄዶ ገደል መግባቱን አትዝንጋ፡፡ ሚስትህን እንደዛ እንዳደረካት ብነግርህ እውነት ነው፡፡ ሜሪ አርምዴ
 ‹‹…የተኛውን በሬ
ጎትጉተው ጎትጉተው አደረጉት አውሬ..›› ብላለች፡፡

   ታግሳ ብታልፍህ እንኳን ስራህ ጀብዱ መስሎህ ትገፋበታለህ፡፡ አሀ! አሁን አንተ በወጣቲኛ አስበሀላ፡፡ እንደ ፔፕሲ ገንፍለህ መደፋት እና መድፋት ላይ በርትተህ እየሰራህ ነው፡፡ ጥንቅሾቹም ሹገር ዳዲ፣ የሆላንድ ላም..መጣ እያሉ አንተ ፊት ሲሆን ፍቅሬ ውዴ…ይሉሀል፡፡ ታዲያ ለአፍ ነው፡፡ ኪስህን እንጂ አንተን መቼ ወደዱና..፡፡ ማን በዛገ ቆዳ ተፈግፍጎ ይወዛል ብለህ ነው? ሚስትህም ነካክተህ ነካክተህ ወይም ጀርባ ሰጥተህ የገፋኸውን ገላ ይዛ ሹገር ማሚ ለመሆን ቦርሳዋን ሞልታ ትወጣለች፡፡ ላስቸግራችሁ ትወጣለችን በሁለት ፍቱልኝ፡፡

   አበበ ተካ በአንድ ዘፈን አልቅሶ አስለቅሶዋችሁ /እኔ አላለቅስኩም/ የቀረው ግማሹም ራሱ ላይ የተጻፈ ግጥም ይዞ ነበር፡፡ ነፍሱን ይማርና ሙሉጌታ ተስፋዬ የሚባል ጓደኛዬ በአንድ ወቅት ሲነግረኝ….
      ‹‹ምንድነው ቀለበት ምንድን ነው ጋብቻ
        በሰማንያ ላይቆም ጎጆና ጉልቻ…›› ያለው አበበ ተካን ታዝቦት እንደነበር አስታቀውሳለሁ፡፡ እኔ ደግሞ ዛሬ ራሳችንን እንድንታዘብ እጽፋለሁ፡፡ ወደ መስመሬ ተመለስኩ፡፡ ልጆቻችሁ ባዶ ቤት ታቅፈው ያድራሉ እናንተ ሹገር ማሚ እና ሹገር ዳዲ ሆናችሁ ሌላ ጠረን ስባችሁ ሌላ ጠረን ታጋሳላችሁ፡፡ ልጆቻችሁ ባዶ ጠረን ስበው ባዶ ጠረን ያጋሳሉ፡፡ በእናትና አባት ናፍቆት ተሰንገው ባዶነት ያዝላሉ፡፡ ምነው ከእናንተ ባልተወለዱ…..አስተውል፡፡ አሁንም ይህ የምልህ ሁሉ እውነት ነው፡፡ ከፈለክ እንከራከር….
 
    እንዲያውም ያደቆነ ሴጣን ሳየቀስስ አይለቅም ይባል የለ ቤት ያለችው ትደብርሀለች እንበል፡፡ ባንልም አጉድላብህ ወይ አጉድለህባት በየአቅጣጫው ሄዳችኋል፡፡ ወጣት መሆን አስኝቶህ ወጣት ማቀፍ ተመችቶህ እንቦቃቅላዋን ልታገባ ልብህ ይከጅላል፡፡ ገንብተህ ያቆየኸውን፣ ያማረብህን ትዳር ትንደዋለህ፡፡ ልጆችህ ይበተናሉ፡፡ ስሜት እንደነዳህ ተነድተህ ስትጋልብ ቤትህን ንደህ ልጆችህን በትነህ የቋመጥክላት ልጅ አንተን ለኪስህ ስትል ታገባሀለች፡፡ ልብ በል ኪስህን እንጂ አንተን አላገባችም፡፡ ከፈለክ ሞክራት ኪስህ ሲወፍር ልታንቆለጳጵስሀለች ኪስህ ሲከሳ ጎልታህ ትሄዳለች፡፡ ያንተን የተሸበሸበ ቆዳ ቆዳዋ ላይ ለጥፋ ስታንቀላፋ የሬሳ መኪና የሆነች ይመስላታል፡፡ ሙት ተሸክሞ ገንዘብ ማግኘት አይደል ስራው የሬሳውስ መኪና፡፡ አንቺም ቢሆን አስተውይ ሹገር ዳዲ ስትይዢ ከሬሳ መኪናው ጋር አንድ ናችሁ፡፡ ካስተዋልክ የሚለዩት የደከመ ስሜትህን ለማጋል በብርጭቆ ወረቀት ጭምር የመፋቅ ያህል ስታሽ መዋሏ ነው፡፡ አሮጌ መኪና አዲስ ሞተር ቢገጠምለት እንኳን ለውጡ ትንሽ ነውና…ብትበላህ እንኳን አፍ የማይደርስበት ብትደርስ አትሞቅም፡፡

   መጀመሪያውኑ በሚስትህ የላከከው ጉድለት ካንተም ሊሆን እንደሚችል ማጣራት ነበረብህ፡፡ አሁን ለአዲሷም አልበቃሀትም፡፡ ራስህን ወጣት ብታደርግም እንደወጣት ለመሆን ብትፈልግም አልሆንክላትም፡፡ በተለይ የማይመቱት ልጅ ሲቆጡት ያለቅሳል እንደሚባለው ሲነኩህ የምትገነፍል ከሆነ ኪስህ እንጂ አንተ ልትደብራት ትችላለህ፡፡

    በቃ!..እሷም ፍለጋው አያልቅም እያለች አምሳያዋን ትኩስ ሀይል ፍለጋ እብስ!....ታዲያ ከአንተ ባገኘችው ገንዘብ ጋብዛና ሸንግላ ነው የምትንጎዳጎደው፡፡ አጋጣሚ ካለ አንተ በትነኸው ከወጣሀቸው ልጆች መካክል አንዱን ይዛ ይሆናል አንተው በሰጠሀት ከእጅህ…ቀን ቀን ልጅህ..አያድርስ ነው ይሄን እንለፈው የማውቀው ታሪክ ግን አለኝ፡፡
  
   እና ወዳጄ እንደነቀነቁት ፔፕሲ በተነካህ ቁጥር አትገንፍል፡፡ እዛው ፔፕሲው ላይ ማስተዋል ያለብህን ልንገርህ? ፔፕሲው ጋዙ እንዳይወጣ፣ እንዳይፈስ/እንዳይገነፍል/ የሚከደነው ከአናቱ ነው፡፡ የሚከፈተውም ከአናቱ ነው፡፡ አንተም ከአናትህ ዝጋና ረጋ ብለህ አስብ፡፡ ወጣት ነኝ ያልከውም ወጣቱ ብትሆን ቴኳንዶ የምትሰለጥነው፣ ትምህርት ቤት የምትገባው፣ ስራ ስርተህ ጥሪት የምታፈራው ወይም ከቤተሰብ የወረስከው ሀብት ከሴት ወደ ሴት የሚገለባበጥ ተልከስካሽ ለመሆን አለመሆኑን ቆም ብለህ ብታስብ ጥሩ ነው፡፡ በዛው ከቀጠልክ አባትህ ሲያደርጉ ያየኸውን ለእናንተ የሰጡትን ቤተሰባዊ ህይወት አንተ ለልጆችህ ካልደገምክ ምኑን ተተካህ..ታስብላለህ፡፡

 በቀረህ፡፡

ወጣትነት እንድታስብበት የሚያደርግህ ብዙ ነገር አለ፡፡ ትላንት አንተ ያጣኸውን የጎደለብህን ቤተሰባዊ ፍቅር ነገ ልጅህ ማጣት እንደሌለበት ማስታወስ አለብህ፡፡ አንተ ባለማግኘትህ እንደተቆጨኸው ሁሉ ልጅህስ ለምን በቁጭት ይደግ..ካልሆነ አትውለድ፡፡ ወልደህ እዚህች ምድር ላይ የምታንገላታው ዘር ከምታፈስ ራስህ ውሀ ብትሆን እና ያለቦይ ጎዳና ላይ ብትፈስ ይሻላል፡፡ ቢያንስ ትንሽም ቢሆን የሚቦነውን አቧራ ትቅንሳለህ፡፡ በቁምህ ቁም ነገር ባትሰራም ሞትህ እንኳን አቧራ ይቀንስ፡፡ ይሄ ካልቻልክ ነው፡፡ ከቻልክ ግን ሰው ሁን፡፡ የአልጋ ታሪክህን ማብዛት፣ ችግርን የሚቋደሱ በችግር የሚጠበሱ ልጆች ጥለህ መለፍ ሳይሆን አንድ ቁም ነገር ሰርተህ እለፍ፡፡ ቁም ነገር መስራት፣ አሻራህን ጥለህ ማለፍ ካቃተህ ታሪክ የሚሰሩ በፍቅር ያደጉ ልጆች ተክተህ እለፍ…አስተውል እስካሁን ያወራነው ሁሉ እውነት ነው፡፡ አይደለም ካልክ እንከራከር፣ እንነጋገር፡፡ እህቴ ሆይ ያንቺን ረስቼው አይደለም እመለሳለሁ፡፡

             ቸር እንሰንብት