ጥበብ እና ፍቅር
ጥበብ እና ፍቅር ያልኩበት ምክንያት በዚህ ዙሪያ በደንብ እንድናወራ በማለት ነው እነሆ እናወራለን፡፡
Thursday, February 28, 2013
ስደት ያደመቀው የሀዘን ከል
ስደት ያደመቀው የሀዘን ከል
ስለልጆቼ ተስፋ
በማጣት በየቀኑ አነባለሁ
በግሩም ተ/ሀይማኖት
‹‹ዛሬ ጨልሟል፡፡
ለእኔ አስከፊ ነገር ነው የሆነብኝ..›› መሰረት የምትባል የመን በጣም ለረጅም ጊዜ በስደት የኖረች የሶስት ልጆች እናት ነች ያለችኝ፡፡
ረጅም ጊዜ የኖረች ግን…ምን ቢገጥማት ነው ይህን ያስባላት?
ከስደትም ስደት አስከፊውን
የአረብ ሀገር ስደት ነው የቀመሰችው፡፡ ከአረብ ሀገርም የመን ከ15 አመት በላይ ኖራለች። የመን ደሞ ጥሩም አለ መጥፎም አለ።
ሞቱም፣ ዱላውም፣ መደፈሩም፣ ማግኘት፣ ማጣቱም ሁሉም አለ። የመንም ይኖራል። እየኖሩ መኖርን የሚጠራጠሩበት ጠብ ሲል ስደፍን
የሚባለውን አይነት ኑሮ ይኖራል፡፡
ይህም ስደት ነው።
የተሻለ ሳይሆን ብዙ ብዙ እውነት የማይመስሉ እውነቶች የተሰገጡበት
ህይወት ነው በየመን ያለው። በተለይ በዚህ ሰዓት እንሰደዳለን…እንደጉድ እንሰደዳለን፡፡ በእርግጥ ችግር የማይነቅለው የለም፡፡
ችግር የማያሰድደው የለም። ኢየሱስ ክርስቶስም ተሰዷል። ነብዩም ተሰደዋል። አረ ቆራጡ እና ተፈጥሮን በቁጥጥር ስር እናውላለን
ያሉት ኮረኔል መንግስቱም ተሰደዋል። እኛ ለስደት አዲስ አይደለንም። አለም ለስደት አዲስ እንዳልሆነ ሁሉ እኛም እየተሰደድን
ነው። ተሰደናልም ገናም እንሰደዳለን። ሀበሻ በየመን እጅጉን አሰልቺ የሆነ ደግሞም ያልሆነ ዝብርቅርቅ ህይወት ከጥሩ ጎኑ
መጥፎው ያመዘነበት ኑሮ መሀል ተሰንጎ ነው የሚኖረው።
በዚህ የህይወት ውጥንቅጥ ውስጥ ከምንኖረው መካከል አንዷ ናት መሰረት፡፡
ዮሴፍ ይባላል ባለቤቷ፡፡ በጤና ማጣት ምክንያት ከቤት ውሏል፡፡ እሷም የመን አረብ ሀገሮችን በነካካው የለውጥ ችግር ውስጥ ባለች
ጊዜ በተነሳው ጦርነት የምትሰራበት ድርጅት ተዘጋ፡፡ አሁን በአነስተኛ ክፍያ ሰርታ ለአፍ ማበሻ ታብቃቃለች፡፡ ዮሴፍ እና
መሰረት ሶስት ልጆች አሏቸው፡፡ ሁለቱ ለትምህርት ደርሰው መማር ከጀመሩ ሰንበት ብለዋል፡፡ ሶስተኛዋ ዘንድሮ ቢሆንም ከመዋዕለ
ህጻናት አልፋ ትምህርት የምትጀምረው እጅ በማጠሩ ምክንያት ሊያስተምሯት አልቻሉም አላሰቡም፡፡ ይማሩ የነበሩትም ዘንድሮ ሊማሩ
ባለመቻላቻው መሰረት ዘውትር በእንባ ትታጠባለች፡፡ አዎ!..ሁለቱም በሚሰሩበት ሰዓት..ጥሩ ገቢ በሚያገኙበት ጊዜ ለትምህርት
የደረሱትን የአስራ ስድስት እና የአስራ ሶስት አመቷን አስተምረዋቸዋል፡፡ ዛሬ ግን ሌሎች ልጆች (ጓደኞቻቸው) ሲማሩ እነሱ ቤት
ሆነው ስደት ያጎናጸፋቸውን.. ስደት ያደመቀውን የሀዘን ከል ለብሰው የሚበሉት ሲጠፋ..ስታይ መሰረት ስታነባ ትውላልች፡፡ እነሱም
ባለመማራቸው ሲያነቡ ይውላሉ፡፡
በእርግጥ ስደት ላይ ያውም ሁኔታዎች ባልተሟሉበት ቀርቶ ደልቶ ሲሳቅም
ከልቅሶ አይለይም፡፡ በሰው ሀገር ተንከራቶ ኖሮ በመጨረሻው ዘመን ነገሮች አጋድለው በችግር መቆራመድን የመሰለ አስከፊ ነገር
የለም፡፡ እባክህ አንድ ነገር አድርግላቸው ብሎ ስለሁኔታው የነገረኝ ይማም የሚባል ሰው ነው፡፡ ምንም ማድረግ ባልችልም ያለውን
ሁኔታ ከመሰረት ጋር ተገናኝቼ አወራን፡፡ መሰረት ለፍታ..ዝቅ ያለ ስራ ሰርታም ቢሆን የሚበሉትን መቻል እንደማያቅታት ነው
የነገረችኝ፡፡ ልጆቹን የማስተማር አቅም አጥታ ማቋረጥ እንደተገደዱ በእንባ ታጅባ ነገረችኝ፡፡ ‹‹ምነው ፈጣሪዬ ሰጥተኸኝ
ለሰዎች ማድረግ በቻልኩ..›› ስል ተመኘሁ፡፡ ግን ምኞት ብቻ ማድረግ ያልቻልኩበት የመከነ ምኞት፡፡ ምን ማድረግ እንደሚቻል
ስጠይቃት ሴሚስተሩ ሳያልቅ እንድታስጀምር ችግሯን አይተው የፈቀዱላት መሆኑን ነገረችኝ፡፡ ወገን ያልሆኑት ችግሯ ተሰምቷቸው ይህን
ካሉዋትወገን አይጨክንም በሚል ተማመንኩ፡፡ የሚያስተምርላት ድርጅቶች ወይም ሊረዱ የሚችሉ በበጎ ስራ ስማቸው የሚታወቅ ሰዎችን
ላናግርላት ግን የምትክፍልበትን ደረሰኝ ማስረከብ እንዳለባት ነግሬ…ቃል ገብቼ ተለያየን፡፡ አጋጣሚዎች ተሰባጠሩና ልበልና
አልገጣጠም ብለው ተላለፉና ደብዳቤ የጻፍኩላቸው ሁሉ ዝምታ ነው መልሴ ብለው ዝምታቸው ውስጥ ተሰነጉ፡፡ በግል የምግባባቸውንም ሰዎች ጠያየኩ፡፡ እነዚህ ስደት አንገት ያስደፋቸው
ህጻናት ነገም አንገት ደፍተው እንዲኖሩ አቅም ያላቸው በጭካኔ ዝምታ ፈረዱባቸው፡፡ እባካችሁ የምትችሉ ሰዎች ለአንድ ዜጋ የሚገባውን
ያህል ትምህርት እንዲያገኙ የምትተባበሩ ካላችሁ መሰረት ብላችሁ 00967713025140 ብላችሁ አግኙዋት፡፡