Friday, September 28, 2012

አፈር ስሆን አልበም እንዳትጋብዢኝ


አፈር ስሆን አልበም እንዳትጋብዢኝ

          በግሩም ተ/ይማኖት

     እዚህ አረብ ሀገር ያሉ እህቶቼ ፎቶ በፎቶ ናቸው፡፡ ወደ ሀገር ቤት ከብር/ዶላር/ ይልቅ የሚልኩት ፎቶ በመብዛቱ በአንድ ወቅት ‹‹የጫዎታ ኩኪስ›› የሚል ቀልድ ያቀረበ አንድ ኮሚዲያን በቀልዱ ላይ ‹‹…ልጄ ፎቶ ላከች..›› ሲሉ አንደኛዋ ሴትዮ ሁለተኛዋ ‹‹..ሁሉም የሚልኩት ፎቶ ነው፡፡ እስኪ አስቀምጪው ድንገት ስትመጣ ትዘረዝረው ይሆናል…›› የሚል ቃላት አካቶበታል፡፡ እውነታነት አለው፡፡ እዚህ የመን ያለ ኢትዮጵያዊ በየቤቱ፣ በየቦርሳው የማየው የፎቶ አልበም ብዛት ምነው ብሩን እንዲህ ቢይዙት፣ ቢያስቀምጡት ያሰኛል፡፡ ከአቅም በላይ ወጪ በማውጣት በፉክክር ሰርግ መደገስ የተለመደ ነገር ሆኗል፡፡ ታዲያ ቀሪው ቪዲዮ ነው፣ ፎቶ ነው፡፡ እግር ጥሎዎት፣ ጥሪ ጎትቶት፣ እክል ገጥሟቸው ለመጠየቅ ቤታቸው ጎራ ካሉ ፈረደቦት፡፡ የአይንዎ ብሌን ተጎልጉሎ እስኪወጣ የፎቶ ክምር ይቀርብሎታል፤ አይንዎ እንኪጠናገር የሚያዩት ቪዲዮ ይከፈትሎታል፡፡

    ታዲያ ምን ቸገረኝ መኮምኮም ነው ካሉ የራስዎ ጉዳይ ራስዎ ይወጡት፡፡ እኔ ግን ስልችት ብሎኛል፡፡ ከሁሉ ከሁሉ ግን የሰለቸኝ ፎቶውን ተከትሎ የሚንጋጋ ቆርፋዳ ወሬ ነው፡፡ አንድ ወዳጄ እና ሚስቱ ከሁለት አመት በላይ ሰርተው ያጠራቀሙትን ገንዘብ አራግፈው ሰርግ ደገሱ፡፡ ሰርጉ ላይ እኔም ነበርኩ ታድሜያለሁ፡፡ ያውም ፕሮቶኮል ነገር ልጠብቅ ብዬ የማልወደውን ሱፍ ሱሪና ኮት ለብሼ እንደ አቅሜ ትከሻዬን ሰብቄያለሁ ምንም እንኳን ወባ የያዘው ብመስልም፡፡ ሰርጉ ባለፈ ሳምንት ስልኬን ከስልኩ የተወረወረ ጥሪ ኮረኮረውና አንቃጨለ፡፡ የመጣውን ድምጽ እንዲያመጣ OK የሚለው ላይ ደነቆልኩት፡፡

  ‹‹ሀሎ!..›› አለኝ ከወዲያ ማዶ፡፡
 
  ‹‹ዛሬ ከሰዓት በኋላ ቤት ነን ና..›› አለኝ እና ከምሰራበት ስወጣ ቤታቸው እንድገኝ ጋበዘኝ፡፡ እዚህ ሀገር ጥሪ ሲኖር ባዶ እጅ አይኬድም ጫት ጠልጠል ይደረጋል፡፡ ግዴታ ባይሆንም እነሱ እያኘኩ በሚያወሩት የምርቃና ወሬ ላለመደንዘዝ ፍቱን መድሀኒት ነው፡፡ ታዲያ ምሳ ከራስህ፣ ጫት ከራስህ፣ ውሀ ከራስህ፣ ሲጋራ ከራስህ፣ የምትፈልገውን ሁሉ ከራስህ…መቀመጫ ከእነሱ ቡና ያጠጡሀል፡፡ ለነገሩ ቡናውንስ ማን አየው? ቡናም የሌለበት… እየቃምክ ተፋጠጥ፣ ቀደዳ ቅደድ አይነት ሴሪሞኒ ያለበትም ቦታ አለ፡፡ ሺሻ አጫሽ ከሆንክ ወረፋህን እየጠበክ ማቡነን ነው፡፡

       እና እላችሁ መቼም ጠሪ አክባሪ ነው ብዬ ጫት አንጠልጥዬ እብስ…የሰርጋቸው እለት የተቀረጸው ቪዲዮ እየታየ ነው፡፡ ሙሽራው ደረቱን ነፍቶ አቀማመጡ ማን እንደ እኔ የሚል ይመስላል፡፡ የሰርጉ እለት ፍርሃት ይሁን ድንጋጤ ዝናብ የመታው ውሻ መስሎ ነበር፡፡ አሁን በሀብታሚኛ ነው የተቀመጠው፡፡  ‹‹ኦ!..የእናቴ ልጅ..እንኳን ደህና መጣህ..የሰርጉን ቪዲዮ እያየን ነው፡፡..›› በማለት ጀመረና በቀጣይ ዙሮች የጉራ ቀደዳው ‹‹…እይ የእኔ ሰርግ እዚህ ሀገር ተስተካካይ የለውም፡፡ ከእነ እከሌ..ከእነ እከሌ ይበልጣል፡፡..ደግሞ እንደማንም ተበድሬ እንዳይመስልህ የደገስኩት፡፡…›› አባባሉ አናደደኝ፡፡ ባዶ ነገር ያዘለ ስሜት ተሰማኝ፡፡ አቅምን ያላገናዘበ ድግሳቸው አቅምን ላላገናዘበ ጉራቸው ሲባል መሆኑ ታወቀኝ፡፡ በዛ ላይ ወደ ሁለት ሺህ ዶላር ብድር ገብቶ መደገሱን እያወቅን ለጉራ መዋሸቱ አናዶኛል፡፡ ቢሆንም ፊልሙን እያየሁ ነው፡፡ ንዴቴ በውስጤ ነው እንዴት ትንፍሽ ልበል? ይሉኝታ የሚባል ገመድ ጠፍሮኝ፡፡ …የሲዲውን ብዛት ተዉኝ፡፡ ከጠዋት ጀምሮ ማታ እስኪተኙ ነው የተቀረጸው መሰለኝ፡፡ ተኝተው የሰሩትንም ቀርጸው አለማቅረባቸው ተመስገን አሰኘኝ፡፡ 

   የዛን ጊዜ የተጀመረው ፊልም እዛ ቤት በሄድኩ ቁጥር ሁሌ እሱ ነው፡፡ ሁሌ እሱ ነው…እንኳን እኔ የቤቱ DVD አስሬ ከሚከፍቱ ከሚዘጉኝ ብሎ በቃሉ አጥንቶ ይዞታል፡፡ ያለ ሲዲ ገና ፓዎር ሲበራ መስራት ይጀምራል፡፡ ሌላ ሲዲ እንደማይገባ አውቆታል፡፡ ሰለቸኝ፡፡ ስልችት ማለት ብቻ ሳይሆን ቅልሽልሽ እስኪለኝ ከሰባት ጊዜ በላይ አየሁት፡፡ በዛ ላይ ማየት ብቻ ቢሆን እኮ ጥሩ ነው፡፡ ይሄ እከሌ ነው ይሄ እየጨፈሩ ነው…የምናየውን ደግሞ ሲነግረን እያየን ነው እስኪ እንይበት ብንል ማን ሊሰማን፡፡ ሌላ ወሬ ከያዝን ፖዝ አድርጎ እዩት እንዳያልፋችሁ ይላል፡፡ ሰው እስኪሰለች እዩልኝን ምን አመጣው?… አሁን ፊልሙን ሽሽት እዛ ቤት እርግፍ፡፡

     ሌላው ደግሞ እጅግ አድርጎ የሚገርመኝ ኢትዮጵያ ፍቅረኛ አላት ወይም አለው ለመባል እዚህ የሚያደርጉት ነገር ነው፡፡ አንዷ ጎረቤቴ የነበረች ልጅ በምንም መንገድም ሆነ በስህተት ስለ ፍቅረኞችም ሆነ ስለ ወንድና ሴት ከተወራ ትጀምራለች፡፡ ‹‹ውይ እኔ እና ተስፍሽ…›› በማለት ትንደረደርና…ማቆሚያ የሌለው የፍቅር ገድል ይተረካል፡፡ ታዲያ መደምደሚያው የመን ስለጠበሰችው ነው፡፡ የሚገርመው ግን  ስለፍቅር እያወሩ ስትመጣ ‹‹መጣች በሉ አቁሙ ሌላ አውሩ..›› የሚሏት ሁሉ አሉ፡፡
   ከጀመረች ‹‹ ተስፍሽ ቦይ ፍሬንዴ….›› የመጀመሪያ መግቢያዋ ነው፡፡ ትንሽ ቆይቶ ቦርሳዋ ይከፈታል ፎቶ ይወጣል፡፡ ያለ ማጋነን ከ50 ጊዜ በላይ ‹‹ቆንጆ›› አይደል? የሚል ጥያቄ ታክሎበት አሳይታኛለች፡፡ ቁንጅናውን እንዳደንቅ ተገድጃለሁ፡፡ ለእኔ ቁንጅናው ያለው ሰው መሆኑ ላይ ነው፡፡ ከእሱ ጋር ስለተዝናኑበት ሆቴል እና መናፈሻ ሁሉ ሲወራልኝ ጆሮዮ እስኪደንዝ ሰምቻለሁ፡፡ ከመስማቴ ብዛት ሚሞሪዮ ሴቭ አድርጎት ገና እሷን ሳይ ያንቃጭልብኛል፣ ያንሾካሹክልኛል፡፡ በመጨረሻ ግን ከእለታት አንድ ጎዶሎ ቀን እኛን እንደ ደቡብ አፍሪካ ከወሬ አፓርታይድ ነጻ የሚያወጣን አጋጣሚ ተከሰተ፡፡ የሰፈሯ ልጅ በእንግድነት መጣችና ፎቶው የአጎቷ ልጅ እንጂ ፍቅረኛዋ አለመሆኑን ፊት ለፊቷ ባለማወቅ በስህተት አጋለጠቻት፡፡ እፎፎፎይ!...ተገላገልን፡፡ ከዛን ጊዜ በኋላ ተሳስታ እጇን ወደ ቦርሳዋ ስትሰድ ‹‹አፈር ስሆን አልበም እንዳትጋብዢኝ እያልኩ አበሽቃት ጀመር፡፡

    ስደት ለውሽት ያመቻል እያሉ ስንቱን ሰማን እባካችሁ፡፡ ኢትዮጵያ እያሉ ፍቅረኛ መያዝ ከአራዳ ልጅ ሊያስቆጥር ነው ወይስ ትሪፐኛ ሊያሰኝ? አንዴ ደግሞ ቅድስት የምትባል ልጅ የገጠማትን ላውጋችሁ፡፡ ኢትዮጵያ እያለች በጣም ቀጭን ነች፡፡ ከቅጥነቷ የተነሳ እንደ ምላጭ ከጎን አትታይም፡፡ ሳሪስ ንፋስ ስልክ ነው የተማረችው፡፡ ወደ የመን ከመጣች 10 አመት አስቆጥራለች፡፡ የአባቷን መሞት ተረዳችና ልናስተዛዝን ሄድን፡፡ ለቅሶ ላይ ሀዘን ማስረሻ ጫዎታ ይደራል፡፡ ጫት ይታኘካል፣ ቡጨቃ ይቦጨቃል፣ ምግብ ይበላል፣ ቆሎ እየተቆረጠመ ቀደዳው ይቀደዳል፡፡ ተረኛ ነኝና…የሚለውን አቀንቅኖ መሀሙድ ኢትዮጵያ ስለነበረች ፍቅረኛው ወሬ ጀመረ፡፡ ታሪኩን ሲተርከው ጥሩ የህንድ የፍቅር ፊልም የሚሰሩ ሁሉ አስመስሎታል፡፡ አንቦ ኢትዮጵያ ሆቴል ስላሳለፉት ደስታ እና ዋና…ሲያወራ ውሸቱን ለማወቅ ጊዜ አልጠየቀብኝም፡፡ ‹‹አንቦ ስንሄድ ሱሉልታ ላይ…›› ሲል አንቦን እንደማያውቀው እየታዘብኩ መሀንዲስ ሳያስፈልገው በሱሉልታ መንገድ ሲቀይስለት ጉዳይ ስለነበረኝ ጥዬ ወጣሁ፡፡ እዛው የቆዩ ልጆች ግን መጨረሻውን ሲነግሩኝ እንኳን በሰዓቱ አልነበርኩ ለእሱ እኔ አፍር ነበር ነው ያልኩት፡፡

    ስለፍቅር ህይወቱ የተቀነባበረ ፈጠራውን ሲነዛባቸው ቆይቶ የኪስ ቦርሳውን መዥረጥ አድርጎ የፍቅረኛውን ፎቶ እዩልኝ በሞቴ አይነት ግብዣውን ያቀርባል፡፡ እየተቀባበሉ ማየት ጀምረው ቅድስቴ እጅ ፎቶው ደረሰ፡፡ ያ-ሁሉ ታሪክ የተወራላት ፍቅረኛ የተባለችው ልጅ ፎቶ የቅድስት ዘጠነኛ ክፍል እያለች ከጓደኞቿ ጋር የተነሳችው ከለር ፎቶ ነው፡፡ ያኔ ቀጭን በመሆኗ አሁን ከመጠን በላይ በመወፈሯ መሀል ነው ለውጡ፡፡

   ‹‹አንተ ይሄማ የራሴ ፎቶ ነው ካንተ ጋር የት ተዋውቀን ነው ፍቅረኛህ የሆንኩት?...›› አስቡት ቤቱ ሁሉ ጸጥ ብሎ ሲሰማ፡፡ ‹‹..ያንቺማ አይደለም..›› ብሎ ሲደርቅ ያዛኑ ፎቶ ኮፒ ከሻንጣዋ አውጥታ ለሰዉ ሁሉ አሳየች አሉኝ፡፡ በእፍረት አንገቱን ሲደፋ አስቤ ወዲያው የብስራት ጋረደው ዘፈን ነው የታወሰኝ ‹‹እኔ አንገቴን ልድፋ ላቀርቅርልሽ..›› የሚለው፡፡ ብቻ ምን አለፋችሁ አሁን አሁን ስለፎቶ እያወሩ ወይ ስለፍቅረኛ እየተወራ ሴቶቹ እጃቸውን ወደ ቦርሳቸው ከላኩ ‹‹አፈር ስሆን አልበም እንዳትጋብዢኝ..›› የምትለውን በውስጤ አንጎዳጉዳለሁ፡፡ አፍ አውጥቼማ እንዳልናገር ይሉኝታ…ፌስቡክ ላይ ይሉኝታ ሜድ ኢን ኢትዮጵያ የሚል ጽሁፍ አይቼ ነበር፡፡ ካገኛችሁት ትክክል ብላችሁ አስምሩበት፡፡ የፎቶው ጉዳይ ወንዶቹም የኪስ ቦርሳቸውን ሲመዙ ‹‹..አፈር ስሆን የተመረጠች የቆንጆ ልጅ ፎቶ ፍቅረኛዬ ነበረች ብለህ እንዳትጋብዘኝ..›› እላለሁ፡፡  ቆይ አረ ሁሉ የቆንጆ..ቆንጆዎችን..ፎቶ እየያዘ ፍቅረኛ ካደረገ ቆንጆ ያልሆነ አይወደድም ያለው ማነው? እንዴ እኛንስ ማን ሊወደን ነው?  
     በመጨረሻም የፎቶ አልበም አለዎት? የት ያስቀምጡታል? ለሰዎች በየትኛው ወቅት ይጋብዛሉ? እነዚህን ጥያቄዎች ያቀረብኩት ያለነገር አይደለም፡፡ እባክዎ ሰው ባልፈለገበት እና በየቦታው አልበም እያወጡ አያሰልቹ ለማለት ነው፡፡

    በሌላ ትዝብት እስክመለስ ጨረስኩ ሰላም እንሰንብት   


Friday, September 21, 2012

በየቤቱ የታደለ የፍቅር ደብዳቤ


በየቤቱ የታደለ የፍቅር ደብዳቤ
    በግሩም ተ/ሀይማኖት
 በጥበብ እና በፍቅር ዙሪያ አንዳንድ ትዝብቶችን ለማስነበብ አስቤ ነው ይህን ለመጻፍ የተነሳሳሁት፡፡ ይህ ብሎግ የተዘጋጀውም በዚህ ዙሪያ ያሉ መልዕክቶችን ለማስፈሪያ ነው እና ገጠመኛችሁን ላኩልኝ፡፡ የየጊዜው ጽሁፎች ቀጥታ እንዲደርስዎ ከፈለጉ ጆይን ዚስ ዌብ የሚለው ላይ ኤሜል አድራሻዎትን ይሙሉ፡፡

    ፍቅር የሚለውን ቃል ታፔላ አድርገው እኩይ ሽምቅ ውጊያ የሚከፍቱ አሉ፡፡ ይቺንም ያችንም ማተራመስ እርድና የሚመስላቸው ሞልተዋል፡፡ ለፍቅር ስለፍቅር ሲሉ የተሰደዱም ገጥመውጣል፡፡ እዚህ የመን ውስጥ ሰሞኑን የገጠመኝን ገጠመኝ ላውጋዎት፡፡ አንድ እንደ እህቴ የምቀርባት ህሊና የምትባል ልጅ የሆነ ቦታ ስትጓዝ ከአንድ ኢትዮጵያዊ ጋር ትገናኛለች፡፡ ልጁ በፈጣን ተናጋሪነቱ ይታወቃል፡፡ ስትነግረኝ ምን ያድረግ ለቃላቶቹ አይከፍልባቸው ዝም ብሎ ሲያወራ ዋለ ተደበርኩበት አለችኝ፡፡ ስሙን ስትነግረኝ አውቀዋለሁ፡፡ በጣም የምወዳት እህቴ ስለሆነች ጉዳቷን ስለማልፈልግ የልጁን መጥፎ እና ጥሩ ባህሪ ዘርዝሬ ነገርኳት፡፡ የማውቀውን ሁሉ አሳወኳት እና ‹‹ሳልነግርሽ ብቀር እና ህይወትሽ ቢበላሽ ህሊናዮን ይወቅሰኛል፡፡ ካወቅሽ በኋላ ምርጫው ያንቺ ነው ብዬ ተውኳት፡፡

       ስልክ ቁጥር ተለዋውጠው ስለነበር መደወል ጀመረ፡፡ ሴቶችን ብዙ ጊዜ ሲያታልላቸው የማየው አፍ ነው፡፡ እሱም ይህን የተረዳ ይመስለኛል በርትቶ አፉን ያሰራዋል፡፡ ወሬው ስለፍቅር ሆኖ ሁለት ነጥብ አራት ነጥብ ወላ ፉልስቶፕ አያውቀውም፡፡ ወሬው ሰለቸኝ በማለት ስልኬ ባትሪ ጨረሰ፣ አሰሪዮ መጣችብኝ… እያለች ስልክ ታጠፋበት ጀመረች፡፡ ከዛም አይነቱ ተቀይሮ ልጅቷ እስኪሰለቻት የፍቅር ቃላት ያዘሉ ሚሴጆች ስልኳን እያንኳኩ መልዕክት ሳጥን ውስጥ ይቀመጣሉ፡፡ ታስነብበኛለች፡፡ ከተላከላት ደብዳቤ ያላነበብኩት አንድም የለም፡፡ ከተለያዩ ቦታዎች የተገለበጡ እንግሊዘኛ የፍቅር ጥቅሶች ሞልተውታል፡፡ እወድሻለሁ …ቅብርጥሴ…ልጅት መልስ አልሰጥም ብላ እኔ ፊት ብትደነፋም ደበቅ ብላ አንዳንዴ ትልክለታለች፡፡

     ወደ ሌላ ታሪክ ልውሰዳችሁ እና አመለወርቅ ትባላለች፡፡ የመን እንደገባሁ በግሩፕ ሲኖሩ ካስጠጉኝ ልጆች አንዷ ነች፡፡ የችግሬ ሰዓት ነች፡፡ ልታገባ ነው ተባለ እና ደስ አለኝ፡፡ ይህን ወሬ እንደሰማሁ ጥቂት ቀናት አልፈውት ያለሁበት ሱቅ ድረስ መጣች፡፡ ልታገባ እንደሆነ መስማቴን እና ደስታዋ ደስታዬ እንደሆነ ገለጽኩላት፡፡ ቅዝዝ፣ ትክዝ..ብላ እሱማ ቀረ እኮ…አለችኝ፡፡ ምክንያቱን እዚህ ጋር ብጽፈውም በማይጠቅም ምክንያት እንደቀረ ስትነግረኝ አዘንኩ፡፡ የሰውየውን ማንነት ስትነግረኝ በአጋጣሚ ህሊና አጠገቤ ነበረች፡፡ ደነገጠች፡፡ በስልክ፣ በSMS መልዕክት አላስቆም አላስቀምት ብሎኝ ቃሉን እስካፈረሰበት ሰዓት ይደውላል ይጽፋል አለችኝ፡፡ ሚሴጁን ልታሳየኝ ፍቃደኛ እንደሆነች ስጠይቃት አሳየችኝ ለአንዷ የጻፈውን ነው መሰለኝ ለሌላዋም የሚልከው ሁለቱም ስልክ ላይ ያለው አንድ አይነት ነበር… ለህሊናም ለአመለም የሚልከው፡፡

       በዚህ ተገርመን በሌላ ቀን ስናወራ አረ ለእኔም ይልክልኛል ብላ ሌላዋም ስልኳን አወጣች፡፡ አላማው ምን እንደሆን ባይገባኝም በየቤቱ የሚታደል የፍቅር ደብዳቤ መሆኑ ገረመኝ፡፡ ይህን ፍቅር እንበለው ልክፍት?    
        ቸር እንሰንብት

Wednesday, September 5, 2012


"አአዩ" የሳምሪፍቅር እና ሀይማኖት
-
በተለይ ለአዋሳ አበባ ፌስቡክ
                      "
በረድኤት መስፍን እንደጻፈው"
     ግሩም ተ/ሀይማኖት
ማሳሰቢያ አንድ፡- ይህ ጽሁፍ የእኔ አይደለም፡፡ ታሪኩንም አላውቀውም፡፡ ግን አውቀዋለሁ-ስላነበብኩት፡፡ ደግሞም ወደድኩት፡፡ ካልወደድኩት መጥላት መብቴ ነው፡፡ ጥላቻ ግን ያለ ምክንያት ሲሆን በሽታ ነው፡፡ ፍቅር ግን አያም አይጎረብጥ ይመቻል፡፡ የረደኤትን መልዕክት በራሴ መስፈርት ለካሁትና ልኬ ሆነ መሰል ወደድኩት፡፡ ፍቅር ፍቅር ይሸታል፡፡ ሸቶም አያበቃ ያውዳልም፡፡ እኔ ደግሞ ጥሎብኝ ፍቅር እወዳለሁ፡፡ ማን እንደሆን የማላውቀው ወይም የማላስታውሰው ሊቅ ‹‹በዚህች አለም ላይ በጣም የምወዳቸው ሶስት ነገሮች ፍቅር፣ ሙዚቃ እና ሴቶች ናቸው ብሏል ብለው ጽፈውለታል፡፡ የውስጤን አውቆ የተነፈሰ ነው የሚመስለው፡፡ ግን ራስ ወዳድ ሆኜ የውስጤን አውቆ አልኩ እንጂ ለሁላችንም ነው፡፡ ከሶስቱ አንዱን የሚጠላ ቢባል አንድም አይገኝ፡፡ ጽሁፉ ፍቅርን፣ ተስፋን፣ ጽናትን፣ እንትንን…የእንትኖች እንትንን ያሳያል፡፡ ይህን ጽሁፍ ያገኘሁት እዚሁ ፌዝቡክ ላይ ነው፡፡ ወዳጄ ረድኤት የተነፈሰው የእሱን ፍቅር ቢሆንም ቁስሌን አኮታል፡፡ የትዝታ ሞተሬን ተረክ አድርጎ አስነስቶት አስጋልቦኛል፡፡ ሳምሪን ከጉያህ ያክርምልህ ብዬ ረገምኩትና መረኩት፡፡ እኔ ደግሞ የቀለም ቀቢ ያህል ቀባ…ቀባ/ይህችን አባባል ወደ ኦሮሚኛ ወስዳችሁ ያዝ..ያዝ ያልኩ እንዳይመስላችሁ/ ጨመርመር አድረጌ አቀረብኩት፡፡ (በ) እዚህ አይነት ቅንፍ ውስጥ ያስቀመጥኩትን ቃላት አደራ በረደኤት ስም አንብባችሁ መልዕክቱን እንዳታዛቡበት፡፡
መሳሳቢያ አንድ፡- በዚህ ጽሁፍ ተሳስበው በትዝታ ስር ቢወድቁ፣ በሰቀቀን እንባ ቢጥለቀለቁ…ሀላፊነቱ የእርሶ እንጂ የጸሀፊው አለያም ያዳማቂው እንዳልሆነ እንገልጻለን፡፡
መሳሳቢያ ሁለት፡- በዚህ ጽሁፍ የተነሳ ፍቅርዎን አስበው የላላውን ወጥረው የተሸነቆረውን ደፍነው፣ የተከፈተውን ከድነው፣ ብርታት አግኝተው ያዘመመ ፍቅርዎን ካዳኑ ፋርማሲ ሳይሄዱ ለሸመቱት መድሀኒት የምንጠይቆት ሂሳብ ድምጽዎን ዝቅ አድርገው‹‹ እልልል..›› ይበሉ፡፡  የቀረውን እናንተ ሙሉት ወደ ንባቡ…….   
       
ወደ ረድኤት ጽሁፍ ስንገባ….
 ሳምራዊት ሰይድን ደሴ አረብ ገንዳ መስጊድ አካባቢ ዞር ዞር ብትሉ አታጧትም፡፡(ሀውልት ሆና እንዳይመስላችሁ) ሰፈሯ እዚያ ነው፡፡ ከመናኽርያው ፊት ለፊት፡፡ ልብን የሚሰረስሩ ዓይኖቿን ሰብራ መንገድ የሚያስተውን ረጅም ጸጉሯን ደብቃ (ሙስሊም ስለሆነች ኢጃብ ስለምትልብስ ነው ፀጉሯ መደበቁ)፤ ሆድ የሚያባባው ፈገግታዋን አምቃ መቅሪብን ለመስገድ በራ ትጠፋለች፡፡ በርግጥ ሳሚሪ ወፍ አይደለችም፡፡ ግን እርግብ ናት፡፡ ይቺ እርግብ ትላንት ወዲያ ወሎ የረሀብ ጠኔ መቷት እፍኝ ጥሬ እና ውሀ አጥታ ዋይ ዋይ ስትል የእኔ ነበረች፡፡ ትላንትም ወሎ የጎሳ ፖለቲካ የታሪክ ቀሚሷን ቀምቶ ሲበጣጥቅባት ከእኔ አልራቀችም ነበር፤ የዛሬዋ ወሎ ግን ከጣቶቼ እያፈተለከች ነው፡፡ (የከፋ ነገር መጥቷል አይንህን ግለጥ ይመስላል ጫወታው፡፡ የመጣውን ሁሉ ዝም ብሎ መቀበል ለእኔ አዋጭነቱ ያጠራጥራል እላለሁ፡፡ ተው!..ማነህ? አላማህስ ምንድን ነው? ከበፊት የሚለየው በምንድን ነው? አግባብ ነው ወይ…ብሎ ማመዛዘኑ ቢጠቅም እንጂ አይጎዳም፡፡ ከቅንፍ ውጡና ወደ ጸሀፊው ሀሳብ ግቡ…) ሀይ...ማኖት የሚሉት የተቀደሰ ነገር ፍቅሬን እየቀማኝ ነው፡፡ ለእኔ ወሎ ማለት ሳምሪ ናት፤ ሳምሪ ማለት ሀገር ናት፤ ሀገር ማለት እኔ ነኝ፤ (ወዳጄ ሀገር ማለት ሁሉ ሲገኝባት፣ ሁሉ ሰላም ሲሆንባት ግሩም ነው…) እኔ ደግሞ ፈርቻለሁ፡፡ ሀይማኖት በፍቅሬ በኩል ሰርጎ እየገባ ሰላሜን ነስቶኛል፡፡
ትዝታ ረሀብና ፍቅር
     1966
.. ነገሌ-አርሲ፡፡ መስፍን ጉተማ ኪሱን በአንድ አንድ ብሮች አጭቆ ይንጎማለላል፡፡ (እህህ!!..ጊዜ ደጉ ያኔ እኮ ሰባቱን አንዳንድ ብር ቢመዙት በግ ይገዛ ነበር፡፡) ከርሱ በላይ ሰው አይታየውም (በሀብታሚኛ እያሰቡ መሆን አለበት)፤ ቁመቱ የረዘመ መስሎታል (መሬት አይንካኝ አለ እንደሚባለው ነው?..)፤ አይኑም ሻሸመኔ ድረስ እንደሚመለከት አምኗል፡፡ ጫማውን ሊያስጠርግ ቁጭ አለ፡፡ ወዲያው አንዲት የዶሮ አይን የምትመስል እንስት በፊቱ ቀርፈፍ ብላ አለፈች፡፡ አባቴ በአይኑ ብቻ አልሸኛትም፡፡ ተከተላት፤ አልፈራም፤ ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት 10 ኩንታል ስንዴ ሽጧላ፡፡ እናም ጠየቃት (ምን በለው? የሚለው የእኛ ጥያቄ ቢሆን መልሱ ምን ይመስላችኋል?) የዛሬዋ እናቴ አልማዝ አራጌ ያን ጊዜ አልችልም የሚል መልስ የመስጠት አቅም አልነበራትም፤ ደክሟታል፤ ረሀብ ጉልበቷን በልቶታል፤ ችግር ወኔዋን ሰልቦታል፤ ሰቆቃ ተስፋዋን አጨልሞታል፤ በርግጥ 66 ርሀብ መዘዝ ለጃንሆይም ተረፏል፡፡ (ኧረ!...ለአንተም ተረፏል፡፡ እህ ምን ነካህ በዛ ችግር ባይሰደዱ የት ተገናኝተው ትወለድ ነበር?..ከእሳቸው ባትወለድ ዘመዳቸውን ጥየቃ ሄደህ ሳምሪን ታገኝ ነበር? ሌላው ቀርቶ ዛሬ ይህን ታስነብበን ነበር...) ቢሆንም ፍቅር መላመድ ነው እንዲሉ ሁለቱም ተዋወቁ፤ ተስማሙ፤ ተዋሀዱ፤ እኔም ወደ ኢትዮጵያ በሰላም መጣሁ፡፡
     2000
.. ደሴ ለአዲስ አመት የእናቴን ቤተሰቦች ለመጠየቅ ላኮመልዛ ደርሻለሁ፡፡ አሁን አይጠገብ ካፌ ቁጭ ብዬ የቁንጅና ማኪያቶዬን አጣጥማለሁ፡፡ እውነቴን ነው ትኩስ ነገር አላዘዝኩም፡፡ ለምን ብዬ እቃጠላለሁ? (በቃ! የአይን ሻወር እየወሰድክ ነበር ብለን እንስማማ?) ሳምሪ ከጓዋደኞቻ ጋር እየተፍለቀለቀች መጣች፡፡ ያኔ እንዲህ ግልጽ ነበረች፡፡ ጸጉሯን አልሸፈነችም፡፡ አይኗን አልሰበረችም፡፡ ደርቄ ቀረሁ፡፡ ይቺ ልጅ ብታምኑም ባታምኑም እናቴን ትመስላለች፡፡ እንደዚህ አይነት ውበት ከእናቴ ሌላ ይኖራል ብዬ አስቤም አልሜም አላውቅም፡፡(ልክ ነህ ወዳጄ ለእኔም ከእናቴ የበለጠ ቆንጆ የለም፡፡ ደግሞም ልክ ነህ ልክ ነኝ እናት ሀገር ናት፣ ሀገር ደግሞ ሳምሪ ናት..) ዛሬ ግን ከእድሜ ልክ እውነት ጋር ተፋጠጥኩ፡፡ ሳምሪን ለመተዋወቅ ከወንበሬ ተነሳሁ፤ ‹‹ወዴት ነው ልጄ?..>> የእናቴ ጥያቄ ነበር፡፡ ወደ ፍቅሬ ልበላት? (እንዴ የምን ወደ ፍቅሬ ነው? ሰው ስጠኝ በልኬ ለሚባለው የተሰጠኝ ከሆነ ልለካ ነው አትልም? ደግሞ የምን ልብ ማንጠልጠል ነው? አገኘሁ አጣሁም አይባልም እንዴ..የትዝታ ኮሮጆዬን የከፈትከው አንዱ እዚህ ጋር ነው፡፡ የወሎ ቆንጆ ጅራፍ አርፎብኛል አንድ በል፡፡ ቤተሰቦቿ ጋር ደሴ ይዛኝ ሄዳለች ሁለት በል፡፡ ሙስሊም ናት ሶስት በል..አረ ስንቱን እኔም ግን እንዳንተ ልዝለለውና ‹‹እንደተመኘኋት አገኘኋት›› የሚለውን አቀንቅኜ ፍሬ ሰጥታኛለች፡፡ ነፍሷን ይማር!!!)
ካምፓስና ፍቅር
2004
. ደብረብርሃን ዩኒቨርስቲ፡፡ ከምማርበት ስድስት ኪሎ በርሬ የመጣሁት ሳሚሪ ናፍቃኝ ነው፡፡ በዚያ ላይ ደግሞ ፈርቻሁ፡፡ እዚህ አዲስ አበባ አወልያ /ቤት የተጀመረው የሙስሊም ወንድሞቼ ተቃውሞ ወደ እኛ ካምፓስ ቀስ በቀስ እየገባ ነው፡፡ ተማሪዎች እየተንሾካሾኩ ማውራት ጀምረዋል፡፡ እየተጠራሩ መውጣት ቀጥለዋል፡፡ እየተሰባሰቡ መነጋገር ይዘዋል፡፡ አልተገረምኩም፤ ማንም ወጣት የለውጥ ማእበል ማስነሳት ይመኛል፤ የለውጡ አካል የመሆን ፍላጎቱም ከፍተኛ ነው፤ ለውጡ ግን አወንታዊ ወይም አሉታዊ ሊሆን ይችላል፡፡ ባለፈው ሳምንት ያየሁት ግን ልቤን ይዤ ወደ ፍቅሬ እንድሮጥ አስገደደኝ፡፡ ፌስቡክ ላይ ተጥጃለሁ፤ የዛሬ ወር አካባቢ አዋሳ አበባ ላይ የጻፍኩትን "ደሴን ያያችሁ" የጉዞ ማስታወሻ ከወደዱት (ላይክ) ካደረጉት መካከል ሀናን አህመድ አንዷ ነበረች፡፡ ያው የደሴ ልጆች ስማቸው አንዱ ከክርስትናው ሌላው ከእስልምናው ይመነጫል፡፡ የሀናንም እንደዚያው ነው፡፡ በዚህች የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ፌስቡክ ገጽ ላይ የተለያዩ የተቃውሞና የአትነሳም ወይ መልእክቶችን አነበብኩ፡፡ ወዲያው በጥያቄ ጎርፍ ተጥለቀለኩ፡፡ ለምን? ምክንያቱ ምንድን ነው? መፍትሄውስ? ይህ መንገድስ ወዴት ያደርሰናል? እመኑኝ ሀናን የመምህር አካለ ወልድ እና የሼህ ሁሴን ጅብሪል ልጅ ልትሆን ትችላለች፡፡ ወይም አቶ አህመድ እና የወ/ ቅድስት (እዚህ ጋር ልብ ያለው ልብ ይበል በጋብቻ፣ በጉርብትና፣ አብሮ በመብላት በጠጣቱ ያልተገናኘ ያልተዋሀደ ማን አለ? ቴዲ አፍሮ ሼመንደፈር ብሎ ያቀነቀነው ያስተዋለውን አስተውሎ ነው፡፡ ወንድሜም ይህን ተረድቶ ካሴቱ እንደወጣ ብዞኛል፡፡ ዝም ብሎ ግብዣ አይደለም፡፡አንቺም በሀይማኖትሽ እኔም በሀይማኖቴ..የሚለውን አስምረንበት እየኖርን ነበረ፡፡ አይ የኔ ነገር ባሶቴን ቀደድኩኝ እኮ ወደ ባለጉዳዩ…)
  ከሳምሪ ጋር ቁጭ ብያለሁ፤
"…
ውዴ ፈራሁ
ለምን ትወደኝ የለ?
አዎ ግንእኮ እተለወጥሽ ነው
ሁላችንም በለውጥ ውስጥ ነን፤ አንተም ጭምር፡፡(በለው!!..አንተ እንኳን ያለወከውን ለውጥ ነገረችህ፡፡ ጓደኛ መስታዎት ነው ማለት እንዲህ ነው..ግን እኮ ልክ ናት ለውጡ ያዝግምም ይፍጠንም ሁሉም በለውጥ ሂደት ስር ተጠልሎ እያዘገመ አለያም እየፈጠነ ነው፡፡)
    ሳምሪ ይሄ ለውጥ ግን አንቺን የሚነጥቀኝ ከሆነ ገደል ይግባ…›› (ይሄ የ2004 ምርጥ አባባል ተብሎ ይመዝገብልኝ፡፡ ሳምሪ ማለት አንተ ነህ፣ አንተ ማለት ሀገር ነህ፤ ሀገር የሚያሳጣ ለውጥ ደግሞ ጥንቅር ብሎ ይቅር፡፡ ህዝብን ከህዝብ፣ ባልን ከሚስት የሚለይ ለውጥ መታሰብም የለበት፡፡ ፍቅርን የሚገል፣ ለጸብ፣ ዱላ የሚጋብዝ ለውጥ ዝቅጠት እንጂ እድገት አይደለም፡፡)
  
ሳምሪ ፈገግ አለች፤ ተጠግታ ሳመችኝ(ይገባሀል በዚህ አባባልህ እኔም የወዳጅ ዘመድ ቦታ ላይ መርቄልሀለሁ)፤ እኔ ቀዝቅዟለሁ(እናቴ..እናቴ እኔን የደብረብርሃን ብርድ እንኳን አንተን ባለ ጸራሙን በግ ያንዘፈዝፈዋል፡፡ በወዳጅነቴ ልምከርህ ቀንደብ የሚያደርጓትን ለመኪና እንደ ቤንዚን የሚያገለግለውን ካቲካላ ብትደራርብ ያንቀለቅልህ ያንበለብልህ ነበር)፡፡ ወደ ዩንቨርሲቲ ለመጀመርያ ጊዜ ስትገባም እንዲህ አይነት ስሜት ተሰምቶኝ ነበር፡፡(እዛው ደብረብርሃን ከሆነ ብርድ ነው በ60 መርፌ ሳይሆን በ60 ዙር አልጋም አይለቅ ቂቂቂቂ…አይ የኔ ነገር አቋረጥ ኳችሁ አይደል…በሉ ቀጥሉ) ጊቢ ውስጥ በተለይ ስለ እኛ የሚወራውን አውቃለሁ፡፡ አብዛኛዎቹ ምክንያት አልባ ነበሩ፤ የተቀሩት መላምቶች ደግሞ ሚዛን አይደፉም፤ ሌሎቹ ግን ከኛው የሚነሱ ናቸው፡፡ (የምን ማለምት? ትቀልዳለህ እንዴ አንዴ በተሳምከው ከቀዘቀዝክ ብትደግምህ ከፈሪጅ ውስጥ የወጣ በረዶ ትሆን ነበርኮ…) ይህ የመርዝ ዝናብ የሳምሪን ልብ እንዳያርስብኝ ፈርቼ ነበር፤ ተሳክቷል፤ ሳምሪ ሚዛናዊ ናት፡፡ የትላንት ሰው አይደለቸም፡፡ እርሷ የነገ ናት፡፡
"…
ለምን መጣህ..ኢግዛም አልደረሰም እንዴ?
ደርሷል..ግን ተጨነኩ አልኩሽ አይደል
እንዴት፤ አሸባሪ ብለው ያስሯታል ብለህ?
አትቀልጂ ሳምሪ..ቀልድ አያምርብሽም ደግሞ ናፈቅሽኝ..
እንዴ፤ የዛሬ ሳምንት አዲስ አበባ አልነበርኩ ..
እኔንጃ በዚህ ቀውጢ ሰአት አብሬሽ መሆን አለብኝ፡፡
ኔቨርተመለስ፡፡ ስሜታዊ እንዳልሆንኩ ታውቃለህ፤ ሀይማኖቴን የምር መያዝና መንከባከብ አለብኝ፡፡ ሊነጥቁኝ የመጡትን አይሆንም እላቸዋለሁ፤ ረዲ በምክንያት ነው፤ በቦንብ አይደልም፤ ሰው በመግደልም አይደልም፤ በማስተማር ብቻ፡፡ ያልገባቸው ብዙዎች አሉ፤ ከእነዚያ ጋር እስክንግባባ ጠብቀኝ፡፡ በኋላ ላንተ ሰፊ ጊዚያቶች ይኖሩኛል፡፡ አሁን ግን ተመለስ፤ ረዲ አንብብ፤ ከዚያም ወደ አርሲ ዘመዶችህ ሂድና የአባትህን ስንዴ እርሻዋች ተንከባከብ…"
ውስጤ እያነባ ተለየኋት፤ ሳምሪ አልሸኘችኝም፡፡ ቀና ብላ አላየችኝም፡፡ እቅፍ አድርጋ አልሳመችኝም፡፡
ተስፋና ፍቅር
ሸገር፤ ስድስት ኪሎ፡፡ ድባብ ቁጭ ብያለሁ፡፡ ከፊቴ የካርል ማርክስ ሀውልት ተኮፍሷል፡፡ (ውይ!...ውይ..ይሄ ጉደኛ እስካሁን አለ? በሞቴ ንገረኝ እስኪ ጺሙን አሁንም አልተላጨ ይሆን? እዛች መናፈሻ ውስጥ ሻይ ስንጠጣ እሱን ማየት ያስጠላኝ ነበር፡፡ የጓደኞቼ ምርጫ እዛ ሆኖ ካልተገደድኩ አልሄድም ነበር፡፡ ስንት ምሁር የሚወጣበት ዩንቨርስቲ በር ላይ የተከሉት ሀገርህ ሀውልት ሊቆምለት የሚችል ምሁር የላትም የታሪክ ሰው የላትም ብለው ለመሳደብ ስለሚመስለኝ እጠላዋለሁ፡፡ ደግሞም ነው፡፡ ይሄው አሁንስ በአፍሪካ ህብረት ጽ/ቤት ጊቢ ጋና ድረስ ሄደው ንክዋሚን ሀውልት ካላቆምንልህ ብለው ሲቀርጹት አጠገባቸው ስላሴ ቤተክርስትያን ያሉት አፄ ኃ/ስላሴን ምን ሰራና ብለው አላራከሷቸውም? የሰው ስናዳንቅ የራሳችንን ረስተን አይደለም እንዴ ቸርችል ጎዳና፣ ባንኮዲሮማ፣ ደጎል አደባባ፣ ስንል የሰነበትነው? ሌኒን ምናችን ሆኖ ነው በሰባት ሚትር ከፍታ ተሰርቶ አዘቅዝቆ ሲያየን የኖረው? ማርክስን ሳይ ይህ ሁሉ ትዝ ስለሚለኝ እጠላዋለሁ…ወዳጄ ድጋሚ ወደዛ ከሄድክ ይህን ሀሳቤን ንገርልኝ፡፡ ለነገሩ አይሰማህም ድንጋይ ነገር ነው፡፡) አየሁት፤ እድለኛ ድንጋይ ነው፡፡ ይሄው ሁለት መንግስታቶችን ለማየት በቅቷል፡፡ (አሁን ሶስት መንግስት ገባ አቶ ሀ/ማርያምንም ጨምርልኝ፡፡ እሳቸው ጊዜያዊ የሚለውን ታርጋ ስለሆነ የለጠፉት ገና አልተደመሩ ይሆን እንዴ?) በመኖርያ ቤቱ ላይ ዩንቨርስቲን የገነባ ንጉስ ሀውልት የሌላት ሀገር በማርክስ ፍቅር ወድቃለች፡፡ ለነገሩ ካርል ማርክስ ቀላል ሰው አይደለም(አዎ ቀላል አይደለም፡፡ እንዴትስ ይቀላል በድንጋዬች የተቀረጸ ድንጋይ አይደለም እንዴ..)፤ አንድ ጊዜ እንዲህ ብሏል አሉ..ሀይማኖትና ኮኬን አደንዛዥ እጽ ናቸው፡፡ ተገርሜም አላባራሁ፡፡(የምን መገረም እግዚሁ ማርህነ..ብረት ነክሻለሁ፡፡ እሱ ሶሻሊዝም የተባለ እጽ ወስዶ ነው..ቢደፍርም) ምን ያለው ደፋር ነው..ጃል!!!!!
    
ባልና ሚስት የሁለት ሀይማኖቶች ውህድ፤ እናትና ልጅም እንደዚያው የሆኑባት ወሎ በሀይማኖት ውጥረት ሰከረች፤ አበደች፤ ጨርቋን ጥላ እርቃኗን ቀረች፤ የመቻቻል ተምሳሌትነቷም ደፈረሰ፤ እንሆ እኛ አዳዲሶቹ ወጣቶች የአባቶቻችንን ቃል ረሳን፤ ምክራቸውን ተጠየፍን፤ ታሪካቸውን ሸሸን፤ ውጭ ውጭውን ተመለከትን፤ ይህም ልባችንን አደነደነው፤ ሞራላችንም ላሸቀ፤ መጪውን ጊዜ መገመት ተሳነን፤ ተስፋችንንም በጡንቻችን ላይ ገነባን፤ እናት ሀገር ጠበበችን፤ እናም ልናፈርሳት ተነሳንግን እኮ ኢትዮጵያ ለሁላችንም ትበቃናለች፡፡
ፍቅር ያሸንፋል ያለው ቴዲ ነው? ከሆነ ጥሩ እንኳንም የኔ ወንድም ሆነ፡፡ አምናለሁ፤ ተስፋም አለኝ..አንድ ቀን ሳምሪ ትመለሳለች፡፡ ከዚያ ከስሜት ጎርፍ ፈንጠር ብላ ትወጣለች፤ እኔም ማተቤን ሳልበጥስ እጠብቃታለሁ፤ ወዲያው ትስመኛለች በጣም ስለናፈኳት ደግማ ትስመኛለች፡፡ ቀጥለን ወደ ጦሳ ተራራ እንሄዳለን፤ በዚያም ከገጠሩ አርሶ አደሮች ጋር ተባብረን የጎመንና የቲማቲም ማሳዋችን እናዘጋጃለን፡፡ ምርታችንንም ደሴ ሰኞ ገበያ ወርደን ለወለዬዎች፤ ለከሚሴ ኦሮሞዎች፤ ለሚሌ አፋሮች እና ለመቀሌ ነጋዴዎች እናከፋፍላለን፡፡ በሌላ ቀን ደግሞ ወደ ትውልድ መንደሬ አርሲ ነገሌ እንመርሻለን፡፡ እዚያ የስንዴ እርሻዎቻችንን እስከ ሲዳማ፣ ጋሞ፣ ወለጋ፣ ነቀምት፣ ጋምቤላ እናስፋፋለን፡፡ ኢትዮጵያንም በስንዴ ዳቦ እናጥለቀልቃታለን፤ የሀገሩ ህጻናት ሁሉ በቀን ሺህ ጊዜ ዳቧቸውን ሲገምጡ እንዲህ እያሉ ያሳታውሱናል.."ይህ እኮ የሳም-ረዲ"ዳቦ ነው፡፡ አዎ ፍቅር የወለደው ዳቦ፡፡
ሳምራዊት መሀመድ እንደሆነች ትላንት የኔ ነበረች፤ ዛሬም የኔ ናት፤ ነገም የኔ ትሆናለች፡፡ ማንም ፍቅሬን ሊነጥቀኝ ከቶም አይችልም፡፡ ሀይማኖት እንኳ! ለዚህ ደግሞ ዋቆም ሆነ ነብዩ መሀመድ ወይም እየሱስ ይረዱኛል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡(አዎ ይረዱሀል የፍቅር አምላክ ናቸውና)

ማስታወሻ -ይህ ጹሁፍ www.one love.com/my land ላይ በእንግሊዘኛ ተለጥፏል፡፡