የምትናደጅ ከሆነ ይህንን እውነታ አታንብቢ
የምትናደጅ ከሆነ ይህንን እውነታ አታንብቢ
‹‹ብልቶቻችሁን
የአመጻ ጦር እቃ አታድርጉ..››
ሐዋርያው
ቅ/ ጳውሎስ
በግሩም ተ/ሀይማኖት
ይሄን ግን ባታነቡት ይሻላል ምንም የማይረባ ነገር ልንገርህ /ልንገርሽ/ ብዬ ባለፈው የጻፍኩ ጊዜ ‹‹እሰይ!!..ወንዶቹን ነገርክልን›› ያላችሁ የሄዋን ልጆች ዛሬ ተረኛ ናችሁ እና ስለእናንተ እናውራ፡፡
በሴቶች ላይ የሚደርስን በደል፣ ሴትነት የሚያመጣውን ጣጣ፣ ያላቸውን ችግር
አስመልክታ ‹‹ማንን ልርገም?›› በሚል ርዕስ እዚሁ ፌዝቡክ ላይ ተከታታይ ፅሁፍ
የምታቀርብ ጸሀይ በየነ የተባለች ጓደኛዬ አለች፡፡ ማንን ልርገም ያለችው ሴቶች ላይ ከሚደርሰው ሳንካ አንጻር ማህበረሰቡን፣
ባህሉን፣ ስንኩል አስተሳሰባችንን ወይስ ሴትንቴን /ሴት መሆኔን/…ለማለት ፈልጋ እንደሆነ እግረ መንገዴን ተንፍሼ ልለፍ፡፡
ታዲያ ሴቶቹም የሚያደርሱትን ጥቃት ግምት ውስጥ ከታ ሚዛናዊ መሆን እንዳለባት አስብ ነበር፡፡ ግን አልጠቆምኳትም፡፡ ያውስ
ሴቶቹ የሚያደርሱት ጥቃት ከላይ እስከ ታች የህይወትን ምህዋር ያናጋ የለ?
ሴት መሆን ጸጋ ነው፡፡ ካወቅሽበት ሴትነትሽን
ካከበርሽውና ካስከበርሳው ጌጥ ነው፡፡ ወንዶች የማያገኙትን የእናትነት ፀጋ ተላብሰሻል፡፡ ካላከበርሽው እና ካላስከበርሽው ግን
ብትወልጅ እንኳን የእናት ቅሌታም ትሆኝና ለልጅሽ ማፈሪያነትሽ ይጎላል፡፡ ልብ በይ የሄዋን ልጅ ሆይ ሔዋን ስሜቷ በነዳት ሮጣ
ቃል ስታ ሞት ብታመጣ ለልጆቿ ሁሉ /ለሴቶች/ መወቀሻ ሆናለች፡፡ አንቺስ ለልጆችሽ መወቀሻ መሆን ትፍልጊያለሽ? በሌላ በኩል
ደግሞ ልብ ልትይ የሚገባሽ በሔዋን የመጣውን ሞት ለማጥፋት መድኃኒቱም የተገኘው ከሴት መሆኑን አትርሺ፡፡ ከድንግል ማርያም ማህጸን
የተገኘው ከስጋዋ ስጋ ከደሟ ደም የተጋራው ነው ያዳነሽ፡፡
ስለዚህ ተፈለኩኝ ብለሽ ሴትነትሽን ከመነዘርሽው፣ በየሱሪው ላይ ከከደንሽው
ሄዋን ስሜቷ በነዳት ሮጣ ቃል ስታ በእጸበለስ ያመጣችውን ሞት ከዝሙት አልጋሽ አፍሰሽ ሞትን ለየሰዉ የምታድይ በሴጣን ግዛት
ያለች ሔዋን ትሆኛለሽ፡፡ እውነት እውነት እልሻለሁ ሴትነትሽን ካከበርሽው አንቺም የተባረክሽ ነሽ፡፡ መድኃኒት የሆነ ባትወልጂም
ፍቅርን የሚሰብክ በፍቅር ያደገ ልጅ ይኖርሻል፡፡ ልጅ ባይኖርሽ እንኳን ቢያንስ በጸጸት ያላደፈ ንጹህ ህሊና ይዘሽ
ትኖሪያለሽ፡፡
በተለይ ያለ እድሜሽ ወጣት ልሁን ብለሽ ባውንድ
እየመዘዝሽ ልጅሽን ልጅሽን የሚያካክሉ ጎረምሳዎች ጠረን ከናፈቀሽ፣ ተጋድመሽ ልታጋድሚቸው ካሰብሽ..ኑሮሽን ናድሽ፡፡ መቼም
አጋድሜ የእናትነት ምክር ልለግሳቸው ነው አትይንም፡፡ አንድ ቀን ትጋለጭና ቤትሽን ስትንጂ፣ ልጆችሽን ስትበትኝ ፀፀት
ሸንቁጦ..ሸንቁጦ ያርመጠምጥሻል፡፡ እድለኛ ካልሆንሽ ጨርቅሽን ጥለሽ..ባትጥይ እንኳን ከእብድ ሳትሻይ ትኖሪያለሽ፡፡
እውነት እንነጋገር ከተባለ ትዳር ላይ ያለ ሰው በሶስት
ምክንያት ነው አይኑን ወደ ውጭ የሚልከው፡፡
አንድ፡- የጎደለ ነገር ካለ ፍለጋ..በተለይ አንቺ
ግለሽ እሱ ከበረደ፡፡ አለያም ከአቅሜ በላይ ነው የሚለውን ካስታወሰሽ….እውነቱ ካልተዋጠልሽ ዞር ብለሽ የልዕልት ዲያናን ታሪክ
ተመልከች፡፡ ልዕልትነቱን ጠልታ ይመስልሻል ወደታች ወርዳ ከሰራተኛዋ ጋር የተንጎዳጎደችው? ከንጉስ ቻርልስ
ያጣችውን እርካታ ፍለጋ ስትማስን የተልሞሰሞሰውን ንጉስ የሚያስንቅ ተገኝቶ ለመሆኑ ፍቺ ስትጠይቅ ያለችውን አስቢ፡፡ ከንጉሱ
ያላገኘችውን በስርቆት ህብረ-አንሶላ ሜዳዋ አፍሳለች፡፡ ታዲያ መስረቅሽም ሆነ መሰረቅሽ በጎ ነው በርቺ እያልኩሽ
እንዳይመስልሽ፡፡ ሌብነትን የሚያበረታታ ቲፎዞ አልሆንም፡፡ ወደ ውጭ ከሚያስኬዱ አንዱ ችግር ይሄ ነው እያልኩሽ ነው፡፡ ታዲያ
በስርቆት መንጎዳጎዱ ሳይሆን በግልጽ መነጋገሩ…ብሎም ችግሩ ካልተፈታ ወደ ስነ-አዕምሮ ጠበብት ብቅ ማለት ነው መፍትሔው ልልሽ
ነው፡፡
ሁለት፡- እሾክን በእሾክ ብለሽ የእሱን እየተሰረቁ መንጎዳጎድ ለመርሳት ወይም ብድር በምድር ብለሽ እሱ በፊት በር
ሲወጣ አንቺ በጓሮ ከወጣሽ ነገር አበላሸሽ፡፡ ማን እሳትን በእሳት ሲያጠፋ አየሽ? እሳትን በውሀ
እንጂ…እሱ እሽኮለሌ ሊል ሲወጣ በ ‹‹እህህ..ታ›› ተሰንገሽ ተርመጥመጭ እያልኩሽ አለመሆኑን ተረጂኝ፡፡ ምን ቆርጦኝ
እላለሁ፡፡ ኑሮን የመምራትም ሆነ የመናድ ብርታት እና ብልሀት ያለው ሴት እጅ ነውና መክረሽም አስመክረሽም መልሺው፡፡ ምን
አጎደልኩ በይው፡፡ ሌላውን ዘዴ አንቺው ፈብርኪው አመሉን ታውቂ የለ?
ሶስተኛ፡- ከሁለቱ ውጭ በሆነ መንገድ አይንሽን ከወረወርሽ፣ እግርሽን ካበደርሽ፣ አፍሽን ካስከደንሽ፣ ጡትሽን
ካስዳበስሽ..የዘማዊነት አመል አለብሽ፡፡ የዘማዊነት አመል ካለብሽና የምትናደጂ ከሆነ ይህን አታንብቢ፡፡ የሌለብሽ ደም ብዛት
ከላይ ታች እንዳይንጥሽ፣ ጨጓራሽን ፈቅፍቆ…በተወደደ ስኳር ስኳር እንዳይጨምርብሽ፡፡ የምናገረው ግን የእውነቶች እውነት ነው፡፡
ካልፈለግሽ አለመቀበል መብትሽ ነው፡፡ እኔ ግን መደባበቅ ይብቃ ብያለሁ፡፡
ፓውደርና ቀለም አድምቆሽ ልጅ የሆንሽ ሲመስልሽ፣ ስሜቱ በነዳው የሚነዳ
ወንድ በአይኑ ሲሸኝሽ..ባየው በር ልግባ የሚል ስሜተ ውሻ ሲጎነታትልሽ ሹገር ማሚነት ካማረሽ ስሜትና ቅሌት ቆመው እየጠበቁሽ
ነው፡፡ የእድሜሽ ጠቋሚ ቀስት ግን ልጆችሽን ድረሽ የልጅ ልጅ ማቀፊያሽ ነው የሚለው ላይ እያመለከት ይሆናል፡፡ ይህን ሰል ግን
ካልወለድሽ፣ ወጣት ከሆንሽ እንደፈለገሽ ሁኚ ለማለት አይደለም፡፡ ሴትነትሽን እንድታከብሪው ነግሬሻለሁ፡፡ የልጆችሽን ፍቅረኛ
በባውንድ እየገዛሽ ስትሻሚ በለገስሽው ፍራንካ ልጅሽን የሚያባልግበት መሆኑን ብታውቂ ምን ይሰማሻል?
መቼም እሰይ ስለቴ ሰመረ ብለሽ አትዘምሪም፡፡ ለንሰሀ ፊትሽን ወደ እግዚአብሄር ቤት ማዞሪያው ሰዓት ላይ ቆመሽ ባሌ ሄደ፣አላየኝም..እርካታን
ከፍንዳታ ፍለጋ ስትሮጪ ‹‹ሰዶምና ገሞራ በእኛ ቤት›› የሚል ድራማ ለመስራት አታስቢ፡፡ በተለይ ልጆችሽ አግቡ የሚለው እድሜ
ላይ ከሆኑ እየተሸማሻቸው መሆኑን ነጋሪ ያስፈልግሽ ይሆን? ለነብስሽ ቤተክርስቲያን ሄደሽ መቋሚያ ለስሜትሽ ጎረምሳ
የምትመረኮዢ ከሆነ እህቴ ሙች አትድኝም፡፡ ዘማዊዋ ሴት በእንባ እግር አጥባ ተፈወሰች እንጂ በዝሙቷ አልተሸለመችም
እኮ!!..ስለዚህ ለልጆችሽም የሀጢያትሽን ውርስ ከምታወርሺ ፍቅርሽን ይራባሉና ስጫቸው፡፡ እርፍ ብለሽ ብትቀመጪ አትገነፍይ፣
አናትሽ ላይ ወጥቶ አያቀውስሽ..ይልቅ መጥፎ ስራሽ ነው ጊዜ ጠብቆ የሚያሳብድሽ፡፡
አበው
‹‹..ጎሽ ለልጇ ስትል..›› የሚሉትን አስቢ፡፡ ባልሽ ጭንቅላቱ ደንዞ ካስማውን ወድሮ ለተከላ ሲቅበዠበዥ በጭኑ ካሰበ
ለልጆችሽ የቀረሽው አንችነሽ፡፡ ለመኖር ምግብ፣ ለነፍስ ጸሎት፣ ለበሽተኛ መድሀኒት..ጉሉኮስና ኦክስጂን..የሚያሰፈልገውን ያህል
ልጆችሽም ሙሉ ሰው ለመሆን ከታደሉ የሁለታችሁም ካልሆነ ያንቺ ፍቅር እንደሚያስፈልጋቸው ለሰከንድ አትርሺው፡፡ አይ እንደ ቦይ
ውሀ ላፈሰሰኝ ሁሉ እፈሳለሁ፤ ለነካኝ ሁሉ እወድቃለሁ ብለሽ ሙዳየ እንቁሽን የትም የወደቀ ቅል ካረግሽው ምነው ካንቺ
ባልተወለዱ፡፡ ፍቅር የተራቡ፣ የፍቅር ድርቅ ያጠቃቸው፣ ቤተሰብ የናፈቁ ልጆች ታፈሪያለሽ፡፡ እነካናዳ፣ እነአሜሪካም ቢሆን
ለምግብ ርሃባችን ስንዴ ይሰጣሉ እንጂ ለቤተሰብ ፍቅር ርሃባችን የሚረዱን የላቸውም፡፡ ያለው አንቺ እጅ ነዋ!!!!
ወጣቷም
ሆንሽ ትልቋ፣ ጎረምሳውም ሆንክ አባት ፍንዳታ ቅዱስ ቃሉ ‹‹ብልቶቻችሁን የአመጻ ጦር እቃ አታድርጉ..›› ማለቱን አስታውሱ፡፡
ስሜተ አፍላዋ እህቴ ብር ብለሽ አትብረሪ..አልጋ ይዘሽ እንዳትቀሪ፡፡
እናቴ ዘመኑ ከፍቷል ከመክፋም ከርፍቷል፡፡ ጤነኛና ጤና ያጣው ተማቷል፡፡ ህይወትሽ ስስ ናት፡፡ አንዴ ካጋደለች ለመመለስ
ትከፋለች፡፡ ያውም ፍሬ ማፍሪያሽ ውስን ናት፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ስደት ላለሽው እህቴ አንድ ገጠመኜን ላውጋሽ እና ልሰናበት፡፡
አንቺ ግን እወቂበት ትምህርት ነው፡፡
የመን እንደመጣሁ አዲስ አበባ የማወቀው አብርሀም የሚባል ልጅ ጋር
ሄድኩኝ፡፡ ሚስቱ የውበት ሳሎን ስላላት ቤት በዋለች ቀን የሴት እድር የሚሰበሰብበት አዳራሽ ይመስላል ቤታቸው፡፡ በሄድኩበት
ጊዜ ጫወታን ጫዎታ ጠለፈውና አንዷ ስንት አመቴ ይመስልሀል? አለች፡፡ መቼም ሴቶች እድሜ ላይ ችግር ነው፡፡ አንዳንዴ
የእናንተ /ሴቶቻችን/ ካላንደር ለብቻ ሁሉ ይመስለኛል፡፡ አንዴ በአንድ ቀን በአንድ ሰዓት አንድ ሰፈር ውስጥ እኩል የተወለድን
መሰሉ አስማማው የምትባል ልጅ ለጓደኞቿ 16 አመቴ ነው ብላቸው እኔን ጠየቁኝ ያኔ 22 አመቴ ነበር፡፡ ነገርኳው፡፡
ውሽታም..ውሸታም ሲሏት ‹‹ዋሽታ አይደለም የእነሱ ቤት ካላንደር ቶሎ ቶሎ ስለማይገለጥ የቆጠረችው የተገለጸውን ብቻ ነው››
ብዬ ማለፌን አስታውሳለሁ፡፡
የማይወዱትን እድሜ ቆጠራ ታዲያ እንዴት እንዲህ አለችኝ አልኩና
ብትናደድም ትናደድ ብዬ እውነተኛ ግምቴን 39ወይም 40 አልኳት፡፡ ‹‹..ውይ ለምን ሚኒስከርት አትገዛልኝም፡፡ ህፃን አደረከኝ
እኮ 56 አመቴ ነው፡፡›› ከምር ደነገጥኩ፡፡ በእንጆ ስጋ ተሰርታ የማታረጅ ሁሉ ነው የመሰለኝ፡፡
‹‹የመን
ብቻ 22 አመት ኖሬያለሁ፡፡››
‹‹ይህን ያህል አመት ቆይተሸ ምን አፈራሽ እስከዛሬ እንደምሰማው እንደሌሎች
ሴቶች ልጅ ብቻ ነው ንብረትም አፍርተሸል?....›› ቤቢ ፊቷን ቋጠረችው፡፡ ‹‹ኡፍፍፍፍፍ…›› ብላ
በረጅሙ ስትተነፍስ ከሱናሚ የተረፈ ንፋስ አሰባስባ የተላከብኝ ይመስል ሊያንገዳግደኝ ነበር፡፡
‹‹እስኪ ተወኝ
ለእኔ ሳይነጋ ጨልሟል፡፡ ገንዘብ ሳሳድድ ሁሉን ነገር ዘንግቼዋለሁ፡፡ ገንዘቡን አግኝቼ በድን ሆኛለሁ፡፡ አንተ ጋዜጠኛ ነህ
ሲሉ ሰምቻለሁ፡፡ ከእኔ ይማሩ ወጣቶቹን ምክራቸው፡፡ በጊዜያቸው ካልተጠቀሙ ህይወታቸው ይበላሻል፡፡ አዲስ አበባም ሰው ቤት
ሰርቻለሁ፡፡ እዚህ ከመጣሁ ስሰራ ቤተሰቦቼም ልለውጥ ስል ቦታ ገዛሁ ቤት ሰራሁ..ወጣትነትም ስለነበር ደስ ይላል፡፡ ያኔ
ፈላጊው ብዙ ነው፡፡ ስትወጣ ስትገባ…ደስ ካለህ ጋር ትዝናናለህ፣ ትገባበዛለህ፡፡ ((ትዝናናለህ፣ ትገባበዛለህ የሚለው በጨዋኛ
አባባል ነው፡፡ ታዲያ ሲመነዘር መዝናኛው፣ መገባበዣ አልጋ ነው ልትል ፍልጋ ነው አላልኩም፡፡ ግን የፍቅር ጠረን እንዳለው
ለማሳየት ነው ድርብ ቅንፍ ያደረኩት፡፡))
..ከስንት ጥረት በኋላ የምፈልገውን አሟልቼ ወልዶ ማሳምን ስናፍቅ ለካ
ረፍዶብኝ ነበር፡፡ ሁሉም በወቅቱ ካልሆነ…አለችኝ፡፡ ለምን ይመስልሻል ይህን ያነሳሁት እታልሜ ወቅትሽን እወቂ ለማለት ነው፡፡
ጨረስኩ አስተውሎ መራመድ ብልህነት ነው፡፡
<< Home