Wednesday, March 20, 2013

የኢትዮጵያ ፊልም እና ቴያትር ከየት ወዴት…..አለ? የለም?



      በግሩም ተ/ሀይማኖት
     ቴያትር በኢትዮጵያ ውስጥ መድረክ ላይ በ1909 እንደተጀመረ ነው የሚነገረው፡፡ ቴያትርን ከመድረክ ውጭ በዚህ ጊዜ ተጀመረ ማለት አይቻልም፡፡ ጥንት ለአደን ሲወጡ ለማጥመድ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ አድነው ሲመለሱ..ብቻ ሰው በባህሉ በእምነቱ የተለያየ ስርዓታዊ ክዋኔ ሲፈጽም፣ በጋብቻ ወቅት..ለጦርነት ሲነሱ የነበረው ፉክራና ቀረርቶ..ሁሉ ቴያትራዊ ሂደት ነበራቸው፡፡ ቴያትር ዘመነ ተብሎ በመድረክ ተከሽኖ ለመጀመሪያ ጊዜ አሁን አንፊ ቴያትር የተባለበት ሴጣን ቤት በመባል የሚታወቀው ቦታ በበጅሮንድ ተክለሀዋሪያት የተደረሰ ቴያትር ቀረበ፡፡ ከዛን ጊዜ ጀምሮ መቶ አመት ያልሞላው የኢትዮጵያ ቴያትር ጥበብ አደገ አላደገም የሚያስብል ደረጃ ደርሶ ይሁን ለማከራከሪያ ብቻ ተፈልጎ ግራ በሚያጋባ ሁኔታ ለብዙ ጊዜ ሲከራከሩበት ያስገርመኝ ነበር፡፡ አላደገም ለሚሉትም አንጋፋዎች ቢሆን ዘመኑ ሲሰለጥን፣ ሲለወጥ የማይለወጥ፣ ቴክኖሎጂ የማይዘልቀው፣ የመከነ ፍሬ አልባ ጥበብ ነው እንዴ ያወረሱን የማያድገው? የማይለወጠው? አልስማማም፡፡ አድጓል፡፡ ይለወጣል፡፡
         ካላደገ እንኳን ተጠያቂ እነሱ ናቸው ማለት ነው፡፡ ምክንያት ጥበብ ብለው ያሳዩን፣ ሲሰሩ ያየነውን የተከተልነው የእነሱ ፈለግ ነው፡፡ የማያድግ የጫጨ ከሆነ ያወረሱንም እነሱ ይጠየቁበት፡፡ በአፋጀሽኝ ‹‹ፋቡላ›› (በእንሰሳት) ቴያትር ተጀምሮ እዚህ ደርሷል፡፡ በእርግጥ ያኔ ለጥበብ ስለጥበብ ተጨንቀው ተጠበው ሲሰሩት ዘንድሮ ለጥበብ ብቻ ሳይሆን ለቀለብም ታስቦ ይሰራል፡፡ ፍራንካዋን ያሰበ ሁሉ ጥሩ አይሰራም ማለት ደግሞ ፈጽሞ ጭፍንነት ይሆናል፡፡
    በመጀመሪያ ደረጃ በተለያየ ወቅት፣ በተለያየ ስልጣኔ፣ በተለያየ ቴክኖሎጂ..የተራራቀን ነገር እንዴት ማወዳደር ይቻላል? በዛን ወቅት ዘንድሮ ያለው ቴክኖሎጂ አልነበረም፡፡ ዘንድሮ ያለው ስልጣኔ፣በትምህርት የተደገፈ ተስዕጦ… ጥበቡም ይህን ያህል ተቀባይነት አልነበረውም፡፡ ይህ ሁሉ ባልተሟላበት፣ ባልነበረበት ሁኔታ ይሰሩ የነበረውን ሲታይ ጥንካሬያቸው የሚደነቅ ነው፡፡ ለዛሬውም መሰረት ሆነዋል፡፡ በእነ አርቲስት ተስፋዬ ሳህሉ (እኛ አባባ ተስፋዬ በሚለው መጠሪያቸው ነው ብዙ የለመድናቸው) በእነሱ ዘመን ሴት ልጅ ወደ መድረክ ብቅ የማትልበት ወቅት ነበር፡፡ እነ  (አርቲስት)አባባ ተስፋዬ የሴት ገፀ-ባህሪያትን ለመሸፈን ሴት ሆነው መድረክ ላይ ይምነሸነሹ ነበር፡፡ አሁን በቴያሩም ሆነ ፊልም ተብሎ በተሰሩት ፊልሞቻችን ላይ ኦርጅናሏን ሴት አቅፎ እየሳመ ሴቷም የራስዋን ጥበብ እየተጠበበች እናያለን፡፡ የዘመን ለውጥ ያመጣው ለውጥ ነው፡፡

      ወንዱ ሴት ሆኖ ሲሰራ እና ሴቷ ራሷ ስትሰራ ማየት ተጽኖስ፣ ለውጥስ አያመጣ ይሆን? ለነገሩ አሁን ደግሞ ሴቷ ጠፍታ ሳይሆን ወንዱ በሰለጠንኩ ባይነት ሴታሴትነቱ ተጣብቶት ተሾርቦ እና ተኳኩሎ ብቅ እያለ ነው፡፡ ጥበብን ለመጠበብ ጸጉርን ማሳደግ እና መኳኳል ግድ ነው የተባለ እየመሰለን ነው፡፡ የጥበብ ሰው ነን ብለው ሲውተረተሩ ከምናያቸው በዛ ያሉት ጉድሮ መሆን ጆሮ ጌጥ፣ መቀባባት… ሴታሴት እንቅስቃሴ ማሳየታቸው ከመብዛቱ አንጻር አብዛኛዎቹ ሜርኩሪ ሆቴል ስብሰባ የጠሩትን ሰዎች (ጌይ) እየመሰሉን ተቸግረናል፡፡ ይህን ባህሪ ስላሳዩ ናቸው ብሎ መደምደም ግን አይቻልም፡፡ አይደሉምም ማለት አይቻልም፡፡  

    አነሳሴ ቅጥ ስላጣው ድርጊታቸው ለማንሳት አልነበረም፡፡ ነገርን ነገር ጠለፈው እና ዘው አልኩበት፡፡ ምን ይደረግ አርቲስት የሀገሩ አምባሳደር መሆን ሲገባው አንገት የሚያስደፋው በዛብኝና ነው፡፡ ለነገሩ በነካ ኮምፒዩተሬ ላይ ሌላ ቀን ሰፋ አድርጌ በዚህ ዙሪያ እተይበዋለሁ፤ እናንተም ታነቡታላችሁ፡፡ አሁን ወደ ተነሳሁበት የፊልም ሂደት ልመለስ፡፡ የቴያትር ጥበብን አደገ አላደገ እያሉ ‹‹ቴያትር ድሮ ቀረ!..›› ሊሉ የሚዳዳቸውን አንጋፋ ተብዬ እድሜ ጠገቦች ያጋጥሙናል፡፡ የዛውን ያህል ‹‹..ያኔ ምን ስራ ሰርተው ነው አሁን ያለነው የምንሰራው እኮ ሪል አርት ነው…›› ብለው ደፍደፍ ያሉባትን ቢጥቂሌ መድረክ ቴሌስኮፕ ከሚያጎላው በላይ የሚያደምቁ፣ መስታዎታቸው የራሳቸውን ካልሆነ ሌላ የማያሳያቸውም ያጋጥሙናል፡፡

    በአንድ ወቅት ቃለ-ምልልስ ስናደርግ ረ/ፕሮፌሰር ሀይማኖት አለሙ ያለኝን ለዚህ ሀሳቤ መደምደሚያ ላድርግ፡፡ በቴያትር ጥበብ ዘርፍ በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ረ/ፕሮፌሰር የሆነው ሀይማኖት አለሙን ‹‹..የቴያትር ጥበብ አድጓል አላደገም ብለው የሚከራከሩ ሰዎች አሉ አንተ የትኛውን ትላለህ?...›› አልኩት፡፡ ‹‹..በጣም አድጓልም አላደገምም ማለት አይቻልም፡፡ ሁሉም የሚለካው በራሱ ወቅት ነው፡፡ ለእነ ዮፍታሄ የእነሱ ዘመን ወርቃማ ዘመን ነበር፡፡ ለእኔ ያ-ያሳለፍኩት ከወጋየሁ ንጋቱ፣ ከደበበ እሸቱ ጋር ደምቀን የነበረበትን ጊዜ እመርጣለሁ፡፡ አሁን ያሉትን ብትጠይቅ ደግሞ ያሉበትን ይመርጣሉ፡፡ ይህን ያልኩህ መብለጡን አለመብለጡን ሳይሆን ሁሉም በዘመኑ መለካቱን ለመግለጽ ነው..›› ብሎኝ ነበር፡፡ ይሄ አድጓል አላደገም ጥያቄ ሲነሳ ብዙ ጊዜ አባቴ እና እኔን የማወዳደር ያህል ነው የሚታየኝ፡፡ በእነሱ ዘመን ገጠር ትምህርቱ የለም፡፡ ቢኖር እንኳን ሲመሽ በኩራዝ ሲያጠና፣ ትራንስፖር የለ…እኔ ስማር ወይም ት/ቤቱ እንደልብ፡፡ በመብራት አጥንቼ..ብዙ ለውጥ አለ፡፡ እኔ የምኖርበት የአሁኑ ዘመን እና አባቴ የኖረበት ትላንትና እንዴት ይወዳደራል፡፡
  ይሄ ቴያትር ላይ የነበረው አድጓል አላደገም ውዝግብ ደግሞ ገና እንደጎረምሳ ፂም በማቀምቀም ላይ ያለው የፊልም ጥበብንም እየነካ ነው፡፡ አድጓል አላደገም የሚል መጠይቅ በተለያ መገናኛ ተነስቷል፡፡ ለመሆኑ ከየት ተነስቶ ነው ያደገው? ከምንም ተነስቶ ማቆጥቆጥ ላይ ከሆነ አላደገም የሚባልበት ደረጃ ይኖር ይሆን? የዛሬ 40 እና 50 ዓመት አካባቢ ፊልም ጭርሱኑ በሀገራችን የተሰራ አልነበረም፡፡ ‹‹ሂሩት አባቷ ማነው?›› የሚለው የመጀመሪያው ፊልም ለሀገራችን ኢትዮጵያ የበኩር ልጅ ሆኖ ተወለደ፡፡ ባለ ነጭና ጥቁር ቀለሙ ይህ ፊልም ፈር ቀዶ ዛሬ ላይ እስክንደርስ አሻራውን አስቀምጧል፡፡
     ለጥቆ ‹‹ ጉማ›› እና ‹‹ፈረንጁ›› ቀጠሉ፡፡ ምንም እንኳን ስሪቱ ኢትዮጵያን ያካተተ ቢሆንም አርቲስት ደበበ እሸቱ፣ ወጋየሁ ንጋቱ፣ ዘነበች ታደሰ /ጭራ ቀረሽ/ እና ሌሎችም የተሳተፉበት ‹‹ሻፍት ኢን አፍሪካ›› ፊልምም ውስን አስተዋጽኦ ነበረው፡፡ ለዛሬው ትላንት መነሻው ነበር፡፡ ስለዚህ አደገ አላደገ የሚለውን ትንሽ ቆይቶ የሚታይ ነው፡፡ እስኪ ከሰዉ ምን ምላሽ አለ? የሚለውን ለማየት ‹‹የኢትዮጵያ ፊልም አድጓል አላደገም?›› የሚል ጥያቄ በፌስቡክ ለቀኩ፡፡ የተሰጠኝን ምላሽ ከትንትና ጋር ለጥቆ አደርሳለሁ፡፡
                 ቸር አንሰንብት

Saturday, March 9, 2013

ሰሜ ባላገርን አጋጣሚ የወለደው ውልደት

ሰሜ ባላገርን አጋጣሚ የወለደው ውልደት   
በግሩም ተ/ሀይማኖት
    አንዳንዴ እንዲህ ነው….ይላሉ፡፡ ይላሉ አልኩ እንጂ እኔ አላኩም፡፡ አልልምም፡፡ ሁሌም እንዲህ ነው በሚለው እስማማለሁ፡፡ ሁሌም አለም በገጠመኞች የተሞላች ናት፡፡ እስማማለሁም አልስማማም ማለት ትችላላችሁ፡፡ ታዲያ በሰለሞን አስመላሽ ስራ ገብቼ እስማማለሁ አልስማማም እያጫወትኩ እንዳይመስላችሁ፡፡ ግን ኬር ተናግሮ ኬር አናጋሪን አብዛልን ነው እና በግጥም ስራዎችዋ የምወዳት ፍጹም አማረ የተባለች ወዳጄ አለች፡፡ አሪፍ ገጣሚ ነች፡፡ ውይ!...ረስቼው ይህን አባባል ተጠቀምኩ፡፡ የአሁን ዕለቱ በቀደም ስለአንዲት ገጣሚ መጽሀፍ ማሳተም በተመለከተ ከአንድ ወዳጄ ጋር ስናወራ አፌን አዳለጠውና…ምላሴ ላይ የሙዝ ልጣጭ ነበረ እንዴ አፌን ያዳለጠው? በቃ! ተዉት አባባል ነው፡፡ እናላችሁ ስለገጣሚዋ ስናወራ የሚለው ላይ ነው አይደል ፖዝ አድረጌ አቅጣጫ የሳትኩት? ተዛው ልቀጥልና ‹‹በጣም እወዳታለሁ›› አልኩት፡፡ ለምን? የሚል ቅናተኛ ጥያቄ ሰነዘረ፡፡ ዝም ብሎ ብወዳት ምናለበት የምወድበት ልብ አነሰኝ አበድረኝ አላልኩት፡፡ ባለኝ ልብ ውስጥ አጨናንቄ የአለምን ህዝብ ሁሉ ብወድበት ምን አገባው? ልቤ ላይ በሊዝ ነው ቦታ የምትገዙት አላልኩ፡፡ ታዲያ እወዳታለሁ ስል ‹‹ለምን?›› የሚያስብል ጥያቄን ምን አመጣው? እጠላታለሁ አላልኩ፡፡
   ለነገሩ እወዳታለሁ ያልኩበት ምክንያት ነበረኝና ‹‹አገጣጠሟ አሪፍ ነው ትገጥማለች›› አልኩት፡፡ ‹‹አሀ! ደርሶህ ነው? ገጥማሀለች?›› አለና ጫዎታዬን በጭንኛ(በወሲብኛ) መነጽር አየው፡፡ ስብዓት ለአብ ማለት ይሄኔ ነው፡፡ ቆይ አረ በቃ ከእንትን ማድረግ ውጭ ዝም ብሎ በእንትን ወዳጅነት የለም? መውደድ አይቻልም? እና አሁንም ፍጹም አሪፍ ገጣሚ ነች ያልኩት ይቀየርልኝና አሪፍ ግጥሞች ትጽፋለች ልበል፡፡ ነገር ተንሸዋሮ ነገር እንዳይፈጥር ጠርጥር ነው፡፡ በአንድ መጣጥፏ ላይ <<ለስንቶቻችን መጥፎ አጋጣሚዎች ጥሩ በረከቶችን አምጥተውልን ያውቃሉ?>> የሚል ርዕስ ሰጥታ መጥፎ ገጠመኞች ጥሩ ማምጣትን በተመለከተ አንስታ ትዝታዬን ኮረኮረችው፡፡ ኮረኮረችው እና ፈነቀለችው፡፡ ብዙ ተመሳሳይ ብጥቅጣቂ እና ብጥሌ ብጥሌ የሚያካክሉ ገጠመኞች ሞልተውኛል፡፡ ይጣፍጥም ይምረርም ገጠመኙን ላገጣጥመው ነው፡፡ ወዳጄ ሙት ቀን ሲገጥምልህ ዝና ወይም ካዝና ቀን ሲጠምብህ ደግሞ አፈር ወይም ካቴና ልታገኝ ትችላለህ፡፡ ሸሩን ትቶ ኬሩን ይግጠመኝ ብለህ ከቤትህ ውጣ፡፡ ድምጻዊ ሰማኸኝ ግን ከቤቱም ሳይወጣ ኬር ስላሰበ ኬሩ መጣለት አጋጣሚዋን ላውጋዎት፡-
     ያኔ የዛሬ ሰባት አመቱ በቀደም ከምሰራባቸው ጋዜጣና መፅሔቶች መካከል አንዱ ለሆነው ዜጋ መፅሔት ጥበብ አምድ ቃለ-ምልልስ ልናደርግ እኔ እና ድምጻዊ ሰማኸኝ በለው በራሱ መኖሪያ ቤት ውስጥ ተገናኝተናል፡፡ ውይ የኔ ነገር እንደድሮው በነጻነት አወራለሁ፡፡ እነዚህ ሜርኩሪ ሆቴል የተሰበሰቡ ሰዎች በተመሳሳይ ጾታ ‹‹እ..እ..እእ….እ...›› እንዳረግ ብለው አይደል ሊያስፈቅዱ የዶለቱት፡፡ ተገናኝተናል የሚለውን በእነሱ ፍላጎት እንዳይመነዝሩብኝ ፈራሁ፡፡ ስለዚህ አባባሌን ልቀይረውና ተቀምጠን እናወጋለን፡፡ ሜዳውም ፈረሱም ያው ተብለን ግን ብቻችንን ወጋችንን መጠረቅ አልቻልንም፡፡ የአዲስ አልበም ስራ ስለነበረው ታዋቂው የባህል ዘፈኖች ግጥም ደራሲ ግሩም ኃይሌ፣ ሙዚቃ አቀናባሪው ሙሉጌታ አባተ፣ ለሰማኸኝ ጥሩ ጥሩ ግጥሞችን የሰራለት ገጣሚ አባተ ማንደፍሮ፣ የሰማኸን ሚስት ገበያነሽ..ሌላ ማን ነበር? ሌላ ማን ነበር?..አዎ ነፍሱን ይማረውና ግሩም ተስፋዬ እህ! ለካ ሶስት ግሩሞች ነበርን…በቃ! ጊዜው ስለረዘመ ረሳሁት የረሳኋችሁ ይቅርታ አለን ብላችሁ እጅ አውጡ...ስሜ ሳይጠቀስ ብላችሁ ሆድ እንዳይብሳችሁ ለነገሩ ፈጣሪ አይርሳችሁ፡፡ ብቻ ተሰባስበን ኦርጋን ይጠቀጠቃል፣ ዜማ ይዜማል፣ ግጥም ይታረማል..ጥሎብኝ ደግሞ የሰማኸኝን ነጎድጓዳማ ድምፅ እወደዋለሁ፡፡ የምንቅም ሰዎች እየቃምን ነው፡፡ ላብ እንጠርጋለን፣ ቡና እንጠጣለን፣ ሲጋራ እናጨሳለን፡፡ በመሀል ላይ የሰማኸኝ በለው ስልክ ደግሞ ደጋግሞ አንቃጨለ፡፡ አነሳው እና ‹‹ሀሎ!›› ሲል ጀመረ፡፡ሁላችንም በትኩረት እንድናዳምጥ በምልክት ነገረን፡፡ - ወቅት ሰማኸኝ ምሽት ከሚሰራበት ሸዋጌጥ ሆቴል /ጭፈራ ቤት/ ወጥቶ የራሱን ጭፈራ ቤት ካሳንቺስ መናኽሪያ ጋር የከፈተበት ወቅት ነበር፡፡

     
ታዲያ ረጅም ጊዜ የሰራበት ሸዋ ጌጥ ሆቴል ሌላ የባህል ሙዚቃ ተጫዋች ተክቶላቸው እንዲወጣ ስለለመኑት አሁን ስሙን ለክብሩ ስል የማልጠቅሰውን ታዋቂ የባል ድምፃዊ ወስዶ ያነጋግረዋል፡፡ በነገራችን ላይ ይህ ስሙን የማልጠቅሰው ድምፃዊ በአንድ ወቅት /ማርያም አካባቢ ቡና ቤት ውስጥ የራሱን ካሴት ከኪሱ አውጥቶ ይከፈትልኝ ብሎ በጥብጦ ሲከፈትለት ለብቻው ሲጨፍር ስላመሸ ዘገባ አድርጌው ነበር፡፡ በራሱ ሂሳብ እየጠጣ በነፃ ጭፈራ ቢያስኮመኩመንም በወራዳ ተግባሩ ተጣልተናል እና ስሙን የማልጠቅሰው በቀል እንዳይመስልብኝም ነው፡፡

    
እናላችሁ ስም አየጠሬ መኮፈስ ይወዳዳል እና እንደለመደው ምሽት ላይ ተቀናጅቶ ለማቅረብ ልምምድ ሊያደርጉ በጊዜ ተሰባሰቡ፡፡ ለቤቱ አዲስ ድምፃዊ ሲንጠባረርባቸው ምን ሆነህ ነው ይልና ኦርጋኒስቱ ሙሉጌታ ቦርጋ ይጠይቀዋል፡፡ እኔ እኮ ታዋቂ ዘፋኝ ነኝ ብሎ የማይሆን ነገር ይናገራቸዋል፡፡ ከመሀላቸው አንዱ….(ማን እንደሰደበው ላለመግለጽ ነው አንዱ ያልኩት)‹‹ሂዲ አንተን ብሎ ታዋቂ ዘፋኝ የሆንክ የባላገር ዘፋኝ..›› ይለዋል፡፡ ይህን ተባልኩ እኔ እዛ አልሰራም ለማለት ነበር ወደ ሰማኸኝ የደወለው፡፡ ይህን የሰማው ሰማኸኝ ታዲያ ምን አለበት ባለ-ሀገር ነን እኮ..እያለ አረጋግቶት ስልኩን ዘጋው፡፡ ሰማኸኝ ባለ-ሀገር!...ባለ-ሀገር!!!! እያለ ሲደጋግም ቆይቶ ባላገር /ባለ-ሀገር/ ማለት ስድብ ነው? እኔ ባላገር ባላገር..ሰሜ ባላገር ባላገር እያለ ያዜም፣ እያጠና በነበረበት ዜማ አንጎራጎረ፡፡ ደስ የሚል ቅላፄ አለው፡፡ ወዲያው ለአባተ ማንደፍሮ እና ለደራሲ ግሩም ሀይሌ እሰኪ ለዚህ ግጥም ስሩልኝ አለ፡፡ ተሰራ ለዝናው እርከን ከፍ ማለት ብቻ ሳይሆን ለእሱነቱ መታወቂያ ሆነው፡፡ ባላገርነት ውበት ነው....ለሰሜ ባላገር