ሰሜ ባላገርን አጋጣሚ የወለደው ውልደት
ሰሜ ባላገርን አጋጣሚ
የወለደው ውልደት
በግሩም ተ/ሀይማኖት
አንዳንዴ
እንዲህ ነው….ይላሉ፡፡ ይላሉ አልኩ እንጂ እኔ አላኩም፡፡ አልልምም፡፡ ሁሌም እንዲህ ነው በሚለው እስማማለሁ፡፡ ሁሌም አለም
በገጠመኞች የተሞላች ናት፡፡ እስማማለሁም አልስማማም ማለት ትችላላችሁ፡፡ ታዲያ በሰለሞን አስመላሽ ስራ ገብቼ እስማማለሁ
አልስማማም እያጫወትኩ እንዳይመስላችሁ፡፡ ግን ኬር ተናግሮ ኬር አናጋሪን አብዛልን ነው እና በግጥም ስራዎችዋ የምወዳት ፍጹም
አማረ የተባለች ወዳጄ አለች፡፡ አሪፍ ገጣሚ ነች፡፡ ውይ!...ረስቼው ይህን አባባል ተጠቀምኩ፡፡ የአሁን ዕለቱ በቀደም ስለአንዲት
ገጣሚ መጽሀፍ ማሳተም በተመለከተ ከአንድ ወዳጄ ጋር ስናወራ አፌን አዳለጠውና…ምላሴ ላይ የሙዝ ልጣጭ ነበረ እንዴ አፌን
ያዳለጠው? በቃ! ተዉት አባባል ነው፡፡ እናላችሁ ስለገጣሚዋ ስናወራ የሚለው ላይ ነው አይደል ፖዝ አድረጌ አቅጣጫ የሳትኩት?
ተዛው ልቀጥልና ‹‹በጣም እወዳታለሁ›› አልኩት፡፡ ለምን? የሚል ቅናተኛ ጥያቄ ሰነዘረ፡፡ ዝም ብሎ ብወዳት ምናለበት የምወድበት
ልብ አነሰኝ አበድረኝ አላልኩት፡፡ ባለኝ ልብ ውስጥ አጨናንቄ የአለምን ህዝብ ሁሉ ብወድበት ምን አገባው? ልቤ ላይ በሊዝ ነው
ቦታ የምትገዙት አላልኩ፡፡ ታዲያ እወዳታለሁ ስል ‹‹ለምን?›› የሚያስብል ጥያቄን ምን አመጣው? እጠላታለሁ አላልኩ፡፡
ለነገሩ እወዳታለሁ ያልኩበት ምክንያት ነበረኝና ‹‹አገጣጠሟ አሪፍ ነው
ትገጥማለች›› አልኩት፡፡ ‹‹አሀ! ደርሶህ ነው? ገጥማሀለች?›› አለና ጫዎታዬን በጭንኛ(በወሲብኛ) መነጽር አየው፡፡ ስብዓት
ለአብ ማለት ይሄኔ ነው፡፡ ቆይ አረ በቃ ከእንትን ማድረግ ውጭ ዝም ብሎ በእንትን ወዳጅነት የለም? መውደድ አይቻልም? እና
አሁንም ፍጹም አሪፍ ገጣሚ ነች ያልኩት ይቀየርልኝና አሪፍ ግጥሞች ትጽፋለች ልበል፡፡ ነገር ተንሸዋሮ ነገር እንዳይፈጥር
ጠርጥር ነው፡፡ በአንድ መጣጥፏ ላይ <<ለስንቶቻችን መጥፎ አጋጣሚዎች ጥሩ በረከቶችን አምጥተውልን ያውቃሉ?>> የሚል ርዕስ
ሰጥታ መጥፎ ገጠመኞች ጥሩ ማምጣትን በተመለከተ አንስታ ትዝታዬን ኮረኮረችው፡፡ ኮረኮረችው እና ፈነቀለችው፡፡ ብዙ ተመሳሳይ ብጥቅጣቂ እና ብጥሌ ብጥሌ
የሚያካክሉ ገጠመኞች ሞልተውኛል፡፡ ይጣፍጥም ይምረርም ገጠመኙን ላገጣጥመው ነው፡፡ ወዳጄ ሙት ቀን ሲገጥምልህ ዝና ወይም ካዝና
ቀን ሲጠምብህ ደግሞ አፈር ወይም ካቴና ልታገኝ ትችላለህ፡፡ ሸሩን ትቶ ኬሩን ይግጠመኝ ብለህ ከቤትህ ውጣ፡፡ ድምጻዊ ሰማኸኝ ግን ከቤቱም ሳይወጣ ኬር ስላሰበ ኬሩ መጣለት አጋጣሚዋን ላውጋዎት፡-
ያኔ የዛሬ ሰባት አመቱ በቀደም ከምሰራባቸው ጋዜጣና መፅሔቶች መካከል አንዱ ለሆነው ዜጋ መፅሔት ጥበብ አምድ ቃለ-ምልልስ ልናደርግ እኔ እና ድምጻዊ ሰማኸኝ በለው በራሱ መኖሪያ ቤት ውስጥ ተገናኝተናል፡፡ ውይ የኔ ነገር እንደድሮው በነጻነት
አወራለሁ፡፡ እነዚህ ሜርኩሪ ሆቴል የተሰበሰቡ ሰዎች በተመሳሳይ ጾታ ‹‹እ..እ..እእ….እ...›› እንዳረግ ብለው አይደል
ሊያስፈቅዱ የዶለቱት፡፡ ተገናኝተናል የሚለውን በእነሱ ፍላጎት እንዳይመነዝሩብኝ ፈራሁ፡፡ ስለዚህ አባባሌን ልቀይረውና ተቀምጠን
እናወጋለን፡፡ ሜዳውም ፈረሱም ያው ተብለን ግን ብቻችንን ወጋችንን መጠረቅ አልቻልንም፡፡ የአዲስ አልበም ስራ ስለነበረው ታዋቂው የባህል ዘፈኖች ግጥም ደራሲ ግሩም ኃይሌ፣ ሙዚቃ አቀናባሪው ሙሉጌታ አባተ፣ ለሰማኸኝ ጥሩ ጥሩ ግጥሞችን የሰራለት ገጣሚ አባተ ማንደፍሮ፣ የሰማኸን ሚስት ገበያነሽ..ሌላ ማን ነበር? ሌላ ማን ነበር?..አዎ ነፍሱን ይማረውና ግሩም ተስፋዬ እህ! ለካ ሶስት ግሩሞች ነበርን…በቃ! ጊዜው ስለረዘመ ረሳሁት የረሳኋችሁ ይቅርታ አለን ብላችሁ እጅ አውጡ...ስሜ ሳይጠቀስ ብላችሁ ሆድ እንዳይብሳችሁ ለነገሩ ፈጣሪ አይርሳችሁ፡፡ ብቻ ተሰባስበን ኦርጋን ይጠቀጠቃል፣ ዜማ ይዜማል፣ ግጥም ይታረማል..ጥሎብኝ ደግሞ የሰማኸኝን ነጎድጓዳማ ድምፅ እወደዋለሁ፡፡ የምንቅም ሰዎች እየቃምን ነው፡፡ ላብ እንጠርጋለን፣ ቡና እንጠጣለን፣ ሲጋራ እናጨሳለን፡፡ በመሀል ላይ የሰማኸኝ በለው ስልክ ደግሞ ደጋግሞ አንቃጨለ፡፡ አነሳው እና ‹‹ሀሎ!›› ሲል ጀመረ፡፡ሁላችንም በትኩረት እንድናዳምጥ በምልክት ነገረን፡፡ ያ- ወቅት ሰማኸኝ ምሽት ከሚሰራበት ሸዋጌጥ ሆቴል /ጭፈራ ቤት/ ወጥቶ የራሱን ጭፈራ ቤት ካሳንቺስ መናኽሪያ ጋር የከፈተበት ወቅት ነበር፡፡ ታዲያ ረጅም ጊዜ የሰራበት ሸዋ ጌጥ ሆቴል ሌላ የባህል ሙዚቃ ተጫዋች ተክቶላቸው እንዲወጣ ስለለመኑት አሁን ስሙን ለክብሩ ስል የማልጠቅሰውን ታዋቂ የባል ድምፃዊ ወስዶ ያነጋግረዋል፡፡ በነገራችን ላይ ይህ ስሙን የማልጠቅሰው ድምፃዊ በአንድ ወቅት ቅ/ማርያም አካባቢ ቡና ቤት ውስጥ የራሱን ካሴት ከኪሱ አውጥቶ ይከፈትልኝ ብሎ በጥብጦ ሲከፈትለት ለብቻው ሲጨፍር ስላመሸ ዘገባ አድርጌው ነበር፡፡ በራሱ ሂሳብ እየጠጣ በነፃ ጭፈራ ቢያስኮመኩመንም በወራዳ ተግባሩ ተጣልተናል እና ስሙን የማልጠቅሰው በቀል እንዳይመስልብኝም ነው፡፡
እናላችሁ ስም አየጠሬ መኮፈስ ይወዳዳል እና እንደለመደው ምሽት ላይ ተቀናጅቶ ለማቅረብ ልምምድ ሊያደርጉ በጊዜ ተሰባሰቡ፡፡ ያ ለቤቱ አዲስ ድምፃዊ ሲንጠባረርባቸው ምን ሆነህ ነው ይልና ኦርጋኒስቱ ሙሉጌታ ቦርጋ ይጠይቀዋል፡፡ እኔ እኮ ታዋቂ ዘፋኝ ነኝ ብሎ የማይሆን ነገር ይናገራቸዋል፡፡ ከመሀላቸው አንዱ….(ማን እንደሰደበው ላለመግለጽ ነው አንዱ ያልኩት)‹‹ሂዲ አንተን ብሎ ታዋቂ ዘፋኝ የሆንክ የባላገር ዘፋኝ..›› ይለዋል፡፡ ይህን ተባልኩ እኔ እዛ አልሰራም ለማለት ነበር ወደ ሰማኸኝ የደወለው፡፡ ይህን የሰማው ሰማኸኝ ታዲያ ምን አለበት ባለ-ሀገር ነን እኮ..እያለ አረጋግቶት ስልኩን ዘጋው፡፡ ሰማኸኝ ባለ-ሀገር!...ባለ-ሀገር!!!! እያለ ሲደጋግም ቆይቶ ባላገር /ባለ-ሀገር/ ማለት ስድብ ነው? እኔ ባላገር ባላገር..ሰሜ ባላገር ባላገር እያለ ያዜም፣ እያጠና በነበረበት ዜማ አንጎራጎረ፡፡ ደስ የሚል ቅላፄ አለው፡፡ ወዲያው ለአባተ ማንደፍሮ እና ለደራሲ ግሩም ሀይሌ እሰኪ ለዚህ ግጥም ስሩልኝ አለ፡፡ ተሰራ ለዝናው እርከን ከፍ ማለት ብቻ ሳይሆን ለእሱነቱ መታወቂያ ሆነው፡፡ ባላገርነት ውበት ነው....ለሰሜ ባላገር
0 Comments:
Post a Comment
Subscribe to Post Comments [Atom]
<< Home