Thursday, June 20, 2013

ጉዞ ወደ ባብ አል-የመን (3)


   ግሩሜን ላዘዝናናው ወጥቼ አራት ኪሎ ሆቴል ጥብስ ስጋብዘው በሞቴ ላጉርሶት እያልኩ ስለምን ዝም አሉኝ፡፡ ግዴለም ይሁን በፍቅር ያለን ተካፍሎ ለመብላት እንጂ ተርፎኝ አይደለም፡፡ ፍቅር ካለ አንድ ጥብስ ለ100 ያጠግባል ብዬ ነው፡፡ ግን ከምር ያጠግባል እንዴ? አዎ፡፡ ብቻላችሁ አጣጣምኩና ውልቅ እንደ አሮጌ ልብስ፡፡ አሮጌ ልብስ ደብሯችሁ አይደል የምታወልቁት፡፡ እኔም ደብሮኝ ነው…ከዛ ወዴት ልውሰደው ጉብኝት አልኩ እና ወደ ባብ አል-የመን አመራሁ፡፡ አጭር ርቀት ቢሆንም ጸሀዩ አናት ቆግቶ ማሰቢያ ያዛባል እና በታክሲ እልም፡፡…
   ኦልድ ሰነዓ ይባላል፡፡ በሌላ አጠራር ባብ አል-የመን (አልባብ) ይሉታል፡፡ ፍሬን ያዝ እናድርግና እዚህች ጋር የተሸለቀኩትን ላስታውሶት፡፡ ገና ሰነዓ እንደገባሁ ባብል የመን ንጉስ አብረሃ..ምናምን ቅብርጥሴ ምንጥሴ…ሲሉ (ቆይ ኧረ!..ምንጥሴ ቅብርጥሴ ብለው ነበር እንዴ? አጋንኜው መሰለኝ፡፡..ቅብርጥሴን ምን አመጣው እዚህ ጋር በየመንኛም ሰራል እንዴ? ብቻ አሉም አላሉም ለማየት ጓጓሁ፡፡ ታክሲ ፍልጋ ወጣሁ በድፍረት ስንትና ስንት ደቂቃ አልባብ..አልባብ.. ሲል ቆሜ እያሳለፍኩ ጸሀይ ላይ እንደ እርጥብ ጨርቅ ዋልኩኝ፡፡ በኋላ ደሜ ፈላና ተንተክትኮ በቃ! በመጣው ታክሲ አልባብ የሚባለው ቦታ ለማየት እብስ….
    እነዚህ አረቦች እንደተሞላ ሰዓት ዝም ብለው ጣጣጣ..አይደል የሚሉት? አንዱ በወሬ ሰነገኝ፡፡ ማነህ? ከየት ነህ? ወዴት ነህ?..ይላል፡፡ ቁም ማነህ አላለኝም እንጂ ክበበው ገዳን አስታወሰኝ፡፡ አንዴማ እንደኩም ፊ ሲያራት…›› አለኝ፡፡ እናንተ ጋር መኪና አለ? መለቱ ነበር፡፡ አየሁት ቁሽሽ ያለ ቶብ ከመልበሱ ጋር እሱም ሌላውን መናቁ አናደደኝ፡፡ ደደብ ማለት በአረቢኛ አላውቀውም እንጂ ያለ ሂሳብ እለቅበት ነበር፡፡ ‹‹ንህነ ኩሉሺ አለምን ለአንቱም›› አልኩት እኔም ላናድደው፡፡ ታዲያ አፈር ስሆን አረቢኛዬን ቂም እንዳይዙባት ያኔ ስለማልችል ነው፡፡ ‹‹..ንህነ አለምናኩም ኩለሺ ለእንቱም..›› ማለት ነበረብኝ፡፡ ደግነቱ ቀይ ስክርቢቶ ይዞ ኤክስ እና ራይት የሚያደርግ የለም፡፡ ለእናንተ ሁሉን ያስተማርን እኛ ነን ማለቴ ነበር፡፡ ግርግር የነገሰበት የእብደት አድባር የወረደበት የሚመስል ቦታ ደረስኩ፡፡ ምንም የሚያምር ነገር የለውም፡፡ ግን ጥንታዊ ቤቶች ተሞሉበት ይመስላሉ፡፡ በምን እንግባባ..በምን እንግባባ የሚለው የማርታ አሻጋሪን ዘፈን በውስጤ እያተጠነጠንኩ…ትንሽ ዞሬ በመጣሁበት ሁኔታ ታክሲዬን ይዤ ምልስ፡፡ አስቡት ብጠፋ ማን ያገኘኛል፡፡ የማርታ ዘፈን ፍቅር መሪ እንጂ ለጠፋ ሰው እቅጣጫ መሪ አይደለም፡፡
   ያስጠጉኝ ልጆች ጋር ገባ ብዬ ቁጭ እንዳልኩ ጆሲ መጣ፡፡ ጆሲ (አህመድ ከሊል) የሙገር ኳስ ተጫዋች ነበር፡፡ ለየመኑ አል-ሒላል ክለብ ተሸጦ የመጣ ተጫዋች ነው፡፡ እናንተዩ ተሸጦ የሚለው ነገር አይደብርም? የባሪያ ፍንገላ ያለ አስመሰለው፡፡ ብቻ ይሁን ገንዘብ ካመጣ እንሸጣለን፡፡ በቀደም እለት ባህር ዳር ኮሌጅ የመርከብ ባለሞያዎች ማስተማር መጀመሩን ተከትሎ የዩኝቨርስቲው ዲን ነው ጂኒ የተባሉት ሰው ስለትምህርቱ ሲናገሩ እናስተምራለን፡፡ የተማሩትን የሰው ሀይል ኤክስፖርት እናደርጋለን፡፡ የውጭ ምንዛሬ ያመጣሉ ሲሉ የነጋዴዎቹ ሚዲያ ETV ሞደርን ስሌቭ ትሬድ ዜናውን አስምቶናል፡፡ ወላዲቴን ራሴ በብረቱ በጆሮዬ ስምቻለሁ፡፡ ከዛ አንጻር የጆሲ የተሻለ ነው፡፡ ብቻላችሁ ጆሲ ሲመጣ ባብል የመን ውሰደኝ አልኩት፡፡ ተያይዘን ውልቅ፡፡      
   በእኔ ቤት አልባብ የሚባለውን ቦታ አይቻለሁ፡፡ አሁን ደግሞ ባብል የመንን ላይ ነው፡፡ ስንሄድ ቀደም ብሎ በሄድኩበት ታክሲ አቅጣጫ ነው የሄድነው፡፡ ከዛ በኋላ በሌላ ታክሲ እንሳፈር ይሆናል ብዬ ስጠብቅ ይሄው አለኝ እና እርፍ….አይ ጆሲ በኳስ ተጫወት ተባልክ እንጂ በግሩም ተጫወት ተባልክ? ጆሲ(አህመድ ከሊል) ባለውለታዬ ነው፡፡ ባለውለታዬ የሚለውን ዘፈን ኤፍ ኤም ላይ ጋብዙልኝ  እባካችሁ፡፡ ምናለበት አትከፍሉ? ኤፍ ኤም ታስከፍል ጀመር እንዴ? ለማንኛውም ተሸልቅቄ በአንድ ቀን ለሁለተኛ ጊዜ የመጣሁበትን ባብ አል-የመን በደንብ ዞሬ አየሁ፡፡ ለነገሩ የሚከፈል ሂሳብ የለበት ኬሚስትሪ….ዞሬ ስንቴ አየሁት..ጎበኘሁት ከዛ በኋላ፡፡
    አሁን በባብል የመን እቅፍ ውስጥ ነኝ ሙቀቷን ሞቄ እምቅ አየሯን ስቤ ጫን..ጫን ልተነፍስ..፡፡ ትርምስ ነው ቢገፉ ምነው ተጋፋህ ብሎ መጠየቅ ያደባድባል፡፡ ዝም አይነቅዝም የሚለውን የተረተው ንጉስ አብርሃ ያኔ ባብል የመንን ሲመሰርት ነው መሰለኝ፡፡ ስለዚህ እኔም ዝም አይነቅዝም ብዬ ግፊያውን ችዬ ላስጎበኞት ነው፡፡ መግቢያው ላይ ሽቶ በገፍ ሞልቷል፡፡ ያለምንም ሀሳብ አንስተው መቀባት ነው፡፡ ይሸጣል ብለው አይስጉ፡፡ እስኪ አንዱን ልቀባችሁ፡፡
            እመለሳለሁ……

0 Comments:

Post a Comment

Subscribe to Post Comments [Atom]

<< Home