ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር በኢቲቪ ውሸት ሲገለጽ.
ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር በኢቲቪ ውሸት ሲገለጽ..
በግሩም ተ/ሀይማኖት
ኢህአዴግ ወቅታዊ የፖለቲካ ትርታውን ለማርገብም ከማክነፍም ኢቲቪን ማራገቢያ
አድርጎ ይጠቀማል፡፡ ኢቲቪ ድራማውን እውን አድርጎ ያቀርባል፡፡ የእመኑኝ ልመናውን ያጧጡፋል፡፡ የኢቲቪ ጋዜጠኞች ደግሞ መጠቀሚያ
ናቸው፡፡ ያውም ከነውሸታቸው፡፡ ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን በተመለከተ በሀድያ፣ ከንባታና ጠንባሮ ህዝብ መካከል ውይይት እንደተካሄደ
ለማሳየት የተቀነባበረ ውሸት በኢቲቪ ትላንት ሰኞ ሐምሌ 7 ቀን ሌሊት ተላለፈ፡፡ የፕሮግራም መሪዋ ጋዜጠኛ መስከረም ጌታቸው በህዝቡ
ፊት ቅጥፈቷን ስትቀጥፍ ህዝቡን አላዋቂ ማድረጓ ገርሞኛል፡፡ ያ- ሞኝ ያደረገችው ህዝብ በአስተያየት መስጠት ወቅት ከእሷ እንዴት እንደሚበልጥ አልተረዳችም፡፡ በመጀመሪያ ዛምቢያ
ላይ ከ40 በላይ ያለቁትን ኢትዮጵያዊያን በተመለከተ ‹‹..እናንተ እኮ ስላላያችሁት ነው እኛ ሄደን እዛው ድረስ ስላየነው…››
ስትል አፈርኩባት፡፡ ቀጠለች እና ልጆቻችሁን አግተው ገንዘብ ላኩ ይላሉ፡፡ ያስልካሉ…ልጆቻችሁ እንደሞቱ እያወቁ ብር ያስልኳችኋል፡፡
ካልተላከላቸው የሀይላንድ ውሀ ላስቲኩን ከፍተው በእዚህ ውስጥ እዩ ይሏቸው እና ከኋላ ከተው አይናቸውን ያወጧቸዋል፡፡ ይሄንን እናንተ
ስላላያችሁ ነው እኛ እዛው ድረስ ሄደን አይተናል…..›› እግዚኦ ማህርነ ክርስቶስ አስባለኝ፡፡
እንዴ እነዚህ ሰዎች በውሸት ተሰንገው ህዝቡንም ውሸት መግበው እስከመቼ
ነው? አንደኛ አይን በዚህ አይነት ሁኔታ እያጠፉ ያሉት የመን ውስጥ ነው፡፡ እነሱ እያወሩ
ያሉት ስለ-ደቡብ አፍሪካ ጉዞ ነው፡፡ ሁለተኛ የመንስ ባይሆን እሷ እዛ ቦታ ሄዳ አይታ የምትመለሰው ማን ስለሆነች ነው? ያን የሚያደርጉት የወያኔ ሰዎች ከሆኑ እና የይለፍ ወረቀት ይዛ ከሆነ ሊሆን ይችላል፡፡ ግን ይህን አላስፈላጊ ውሸት መዋሸቱ ለምን አስፈለገ? የዘሬን ብተው ያንዘርዝረኝ
እዛም ውስጥ መኖሩን እናውቃለን ከሊቅ እስከደቂቅ ሲዋሹን ኖረዋል፡፡ እዚህ የመን ውስጥ ያሉት አፋኞች ጋር ከሆነ ግን ቦታው ላይ
እንኳን እሷ ቀርቶ የሀገሩ ተወላጅ የሆኑ ጋዜጠኞችም ሆነ ወታደር እና ባለስልጣናት ድርሽ አይሉም፡፡ ታዲያ ለፖለቲካ መጠቀሚያ መንግስትን
ለህዝቡ አሳቢ ለማስመሰል ሀገር የሚያውቀውን እውነት ዋሽቶ ለማሳመን መጣር ነው፡፡ ልጅቱ ፈጽሞ በጉዳዩ ላይ ብቃትም ሆነ ብስለት
ሳይኖራት በሰባኪ ካድሬነት ብቻ ዝግጅቱን መምራቷ ያስታውቃል፡፡ ምክንያቱም ስለዚህ ሁኔታ በተከታታይ ከየመን ስዘግብ እኔ ነኝ ልጁን
ያናገርኩት (ቃለ-ምልልስ ያደረኩት) እሷ ከየት መጥታ እንዳየችው አላውቅም፡፡
ቀጠለች ረኸጥ በሆነ አገላለጽ ‹‹እየተጎዱ ያሉት የእናንተ ልጆች ናቸው፡፡
እኛ ምን ሆንን ከአዲስ አበባ የሚሄድ የለም ስለዚህ የእናንተ ልጆች ናቸው የተጎዱት ስለዚህ ደላላቹን ጠቁሙን ….›› አስቡ አንድ
የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ጋዜጠኛ ክፍፍል ገብታ እናንተ ናችሁ የተጎዳችሁት እኛማ ምን እንሆናለን…ስትል፡፡ የእነሱ መጎዳት ጉዳቷ
ያልሆነች ድንግዝግዙ የወጣባት ጸለምተኛ ሆና ስትታይ፡፡ በዛ ላይ ሰዉ እየነገራት ያለውን ያልተረዳች ግብዝ ነች፡፡
‹‹…እኛው ይዘናቸው ነው ያለነው፣ ደላላዎቹ እኛው ራሳችን የመረጥናቸው
ያቀፍናቸው…›› ልክ ነበሩ፡፡ እንኳን እነሱ እኛ እዚህ ሆነን የምናውቀውን የሀዲያ ዞን የፖሊስ ባለስልጣን ሰዒድ በሚል ስም በድለላው
የሚታወቅ ሰው እንዴት አድርጎ ህዝቡ ይጠቁም?
ይሔን ውይይት የጠሩት ለይስሙላህ ብቻ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ አብተው የተባሉት
የከንባታ ጠንባሮ ዞን አስተዳዳሪ እና ማቲያስ የተባለ የሀዲያ ዞም አስተዳዳሪ ህዝቡን ከማስፈራራት ባልተናነሰ አፍጥጠው ጠቁሙ ይላሉ፡፡
መንግስት በአንድ ቅስቀሳ ማዳን እንደማይችል ያውቃሉ፡፡ ጊዜያዊ ፖለቲካ ሽፋን መስጫ ይጠቀማሉ፡፡ ግን እስከመቼ እንወሻሽ?