Friday, August 23, 2013

አሸንድዬ በዓል በላሊበላ

  • የጽሑፍ መጠን የጽሑፍ መጠን ይቀንሱ የጽሑፍ መጠን ይጨምሩ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አማኞች ዘንድ የጾመ ፍልሰታ ለማርያምን ፍጻሜ ተከትሎ የሚከበረው የአሸንድዬ በዓል በዋናነት በሰሜን ኢትዮጵያ ከሚከበሩ መንፈሳዊ በዓላት መካከል የሚጠቀስ ነው፡፡
በትግራይ፣ ዋግና ላስታ ከሚከናወኑ በርካታ ሃይማኖታዊ ባህላዊ ጨዋታዎች መካከል እንደ እሽውላሌ፣ ጊጤ፣ ገና ጨዋታ፣ አሸንድዬ፣ ሙሻሙሾ እና ሆያ ሆዬ የመሳሰሉት በዓላትም በዐበይትነት ይጠቀሳሉ፡፡ በነሐሴ ወር አጋማሽ ከቅድስት ድንግል ማርያም በዐለ ዕርገት/ፍልሰታ/ ጾም ፍች ጋራ ተያይዞ የሚከበረው የአሸንድዬ በዓል ማራኪና ልዩ ባህላዊ ጨዋታ ነው፡፡
በቀድሞዋ ሮሃ በኋላ ላሊበላ የሚከበረው በዓሉ፣ በላስታ “አሸንድዬ”፣ በትግራይ “አሸንዳ”፣ በዋግ “ሻደይ”፣ በራያ ቆቦ “ስለል በይ” በመባል ተቀራራቢነት ባላቸው ስያሜዎች ይጠራል፡፡ በሁሉም አካባቢዎች በተመሳሳይ ወቅት ልጃገረዶች ከወገባቸው ላይ ሣር መሰል ቅጠል በማሰር ከቤት ቤት በመዘዋወር የተለያዩ ጣዕመ ዜማዎችን በማሰማት የሚጫወቱት ጥንታዊ፣ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ጨዋታ ነው፡፡ ዘንድሮም ከላሊበላ በተጨማሪ በላስታ እና በመቐለ በደማቅ ኹኔታ ይከበራል፡፡
በትግራይና በአማራ ክልል የሚከበረው ይኸው በዓል በተለይ በዚህ ዓመት በላሊበላ በታላቅ ድምቀት እንደሚከበር ታውቋል፡፡ የቅዱስ ላሊበላ ደብርን ጨምሮ የወረዳ ቤተ ክህነቱን በበላይነት በሚመራው የቅዱስ ላሊበላ ደብር አስተዳደር ካህናት የሚሳተፉበት ያሬዳዊ ዝማሬና ቅኔ የበዓል ዝግጅቱ አካል ሲኾን የበዓሉ መክፈቻ ሥነ ሥርዐት በሚካሄድበት ነሐሴ 16 ቀን 2005 ዓ.ም. ሽት የላስታ ላልይበላ ሕዝባዊ ባህል የኾነው የአሸንድዬ ልዩ ልዩ ባህላዊ ጨዋታዎችም ይቀርቡበታል፡፡
በዓሉን መሠረት ያደረጉ ጥናታዊ ጽሑፎች በባለሞያዎች ቀርበው የፓናል ውይይት እንደሚካሄድ ለበዓሉ አከባበር ከወጣው መርሐ ግብር ለመረዳት ተችሏል፡፡ ከነሐሴ 15-17 ቀን 2005 ዓ.ም. በሚቆየው ክብረ በዓል ከክልልና ከፌዴራል መንግሥት የተወጣጡ ከፍተኛ ባለሥልጣናትን ጨምሮ 200 ያህል ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እንደሚገኙበት ተዘግቧል፡፡
በዓሉ ባህላዊና መንፈሳዊ ይዘቱን ጠብቆ ተጨማሪ የቱሪስት መስሕብ እንዲኾንና የባህል ገጽታ ግንባታን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ በከተማው አስተዳደርና በክልሉ መንግሥት ትኩረት መሰጠቱ በክልሉ የቱሪስቶችን ቁጥር እንደሚያሳድገው ብዙዎች ይናገራሉ፡፡
በላሊበላና አካባቢው የቱሪስት ፍሰቱ ከፍተኛ የሚኾነው በታኅሣሥና በጥር ወራት ሲኾን ይህም በአብያተ መቅደሱ (በቋሚ ቅርሱ) የሚከበሩ በዓላትን ማእከል ያደረገ ነው፡፡ ባህላዊና ሃይማኖታዊ ቅርስ የኾነው የአሸንድዬ በዓል በአግባቡ ታቅዶና ተደራጅቶ ለቱሪስቶች ቢተዋወቅ ደግሞ በነሐሴና በመስከረም ወር የቱሪስት ፍሰቱን በመጨመርና የጎብኚዎችን ቀልብ በመሳብ የቱሪስቶችን ቆይታ ያራዝማል፡፡ ይህም እንደ ቻይና የውኃ በዓል፣ እንደ ስፔን የኮርማ ውጊያ፣ እንደ ብራዚልና አርጀንቲና የጎዳና በዓል ለመልካም ገጽታ ግንባታ ሊውል፣ ኢንቨስትመንትን ሊያስፋፋና የሥራ ዕድል ሊጨምር ይችላል፡፡
የአሸንድዬ ባህላዊ ጨዋታ መገለጫ የኾነው አሸንዳ እንደ ቄጤማ ረዥምና እንደ ቅጠል ሰፋ ያለ ነው፡፡ ቁመቱ ከ80 እስከ 90 ሣ.ሜ ይኾናል፡፡ ለምለም ነው፡፡ በወገብ እንደ ሽብሽቦ ኾኖ ይታሰርና ከግጥሙና ከዜማው ጋራ ተዋሕዶ በዳሌያቸው ላይ ይዞራል፤ ይሽከረከራል፡፡ በተለይ፡-
“እቴ አይዞርም ወገብሽ
ባቄላን ነው ቀለብሽ”
እያለች የበለጠ ወገባቸው እንዲዞር በግጥምና በዜማ አውጭዋ ስታዜም ተቀባዮቹ ደግሞ አባባሉን ለማስተባበል በኃይልና በዘዴ ወገባቸውን ሲያዞሩ ቅጠሉ ርግፍ እያለ ከወገባቸው ጋራ ይሽከረከራል፡፡
“አሸንዳዬ አሸንዳ አበባ
እሽርግፍ እንደወለባ”
ሲሉና ሲዞሩም አብሮ በኃይል ይዞራል፤ ከወገባቸው ላይ ርግፍ ይልና ዞሮ ተመልሶ ያርፋል፡፡ አሸንድዬ በተለያዩ የሰውነት አካላት (በአንገት፣ በትክሻ፣ በወገብ፣ በእጅ፣ በእግር ወዘተ) እንቅስቃሴ ይከወናል፡፡
አንዳንድ ምሁራን አሸንድዬ ገና ቅድመ ልደተ ክርስቶስ ጀምሮ የክረምቱን (ጨለማው፣ ጭቃው፣ ጎርፉ፣ ዶፉ፣ ብርዱ) መውጣትና የበጋውን (ብርሃኑ፣ ፀሐዩ፣ የወንዙ ጥራት፣ የአዝርዕቱ ማሸት፣ የአበባው ማበብ) መግባት ምክንያት በማድረግ ደናግል (አዋልድ) ቅድመ ዕንቊጣጣሽ ሁለት ሳምንት ሲቀረው ጀምሮ አዲሱን ዘመን በደስታና በሐሤት ለመቀበል በብሩህ ተስፋ ውስጥ ኾነው ይጫወቱት እንደነበር ይናገራሉ፡፡ 

Monday, August 19, 2013

ቡሄ እና ትዝታው

 
በግሩም ተ/ሀይማኖት
አንዳንዴ ትዝታ በትዝታ ማህደር ውስጥ እንዳዳፈኑት እሳት ተዳፍኖ  እንዳይቀመጥ የሚቀሰቅስ አይጠፋም፡፡ የቡሄ ትታዬን ልከትበው ባላስብም የወዳጄ ፋሲል ተካልኝን ጽሁፍ ሳይ የተዳፈነው አልዳፈንም ብሎ አደባባይ ሊወጣ መጣ፡፡ የመጣውን ጻፍኩት፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ፋሲል ‹‹..ስደትን በማባባስ..ዋና ተጠያቂው መንግሥት ቢሆንም..ጠንሳሾቹና አነሳሾቹ ግን...ቡሄ ጨፋሪዎች ይመስሉኛል::...(አቅም እንደሌላቸው ስለማውቅ ነው - ተጠያቂ ያደረግኩዋቸው:: ማንም በአቅመ-ቢሱ ላይ
ይበረታል አይደል?!?...)ለማንኛውም ቡሄ ጨፋሪዎቹ :-

"...
እዛ ማዶ አንድ ኮንጐ..
እዚ ማዶ አንድ ኮንጐ..
የኔማ እንትና..ሊሔድ ነው ቶጐ::"
...
እያሉ::……….›› ብሎ ያሰፈረውን ሳይ የቡሄ ጭፈራ እንዲህ ቅጡን ሳያጣ አንዴ በልጅነቴ  ጨፍሬ ነበር፡፡ ዛሬ ነበር ላይ ሆኜ እቆዝማለሁ፡፡ ምን እኔ ብቻ..እናንተም ጭምር ሆነን እንቆዝማለን፡፡ ሴቶችም አበባየሆሽ  አልፎባችሁ ነበር ላይ የትዝታ ማህደራችሁን የከፈታችሁ አንድ ሆነናል አይዟችሁ፡፡ …ታዲያ መለስ ብዬ የትዝታ ማህደሬን ስቃኘው አንዴ ብቻ የጨፈርኩበት የቡሄ ትዝታ ሌላ ጊዜ ተመልካች አድርጉኝ ጥሎብኝ ያለፈውን ጉልህ ታሪክ እንሆ፡-
   አሁን ማን የሙት በልጅነት ዘመንህ አንዴ ብቻ ነው ሆያ ሖዬ ያልከው ትሉኝ ይሆናል…ይሁን በሉኝ፡፡ ግን እናቴ ከነበራት ጥላቻ አንጻር እኔም ሆንኩ እህቴ ለቡሄም ሆነ ለእንቁጣጣሽ..አይፈቀድልንም፡፡ እህቴ ከነአካቴው አበባየሆሽ ያለች አይመሰለኝም፡፡ እናቴ እንዳልጨፍር ከምትሰጠኝ ምክንያት ውስጥ ድሮ ለበአሉ ነበር ጭፈራው አሁን ለገንዘብ ነው፡፡ ልመና ደግሞ ለእኛ ቤት አልተፈቀደልንም፡፡ እድልም የለንም፡፡…የመሳሰለ ብዙ ምክንያት ትደረድራለች….ደጉ ዘመን ነገር የማያንሸዋርሩበት ጊዜ ሆኖ ነው እንጂ ልመና ለእኛ ቤት አልተፈቀደም..ስትል ለሌላው ተፈቅዷል ወይ ብለው ጸብ ያለሽ በዳቦ….(ኤጭ!!!!...ዛሬ እንኳን እስኪ ጸብ ያለሽ በሙልሙል እንበል…ቡሄ አይደለ?) በቃ!..ሁሌ ቡሄ አትጨፍር ስባል በጉጉት ተወጥሬ እከተላቸው እና በርቀት ሲጨፍሩ አያለሁ፡፡ አንዴ ነሸጥ አደረገኝ እና እኔም አለሁብት ብዬ ስጨፍር ዋልኩ፡፡ ወንደሰን ሰብስቤ…ነብዩ ሀይሉ…ዳንኤል መሀሪ…ሌላ ማን ነበር? አስታውሱኝ እስኪ..ቅድስተ ማርያም ነን ያላችሁ እስኪ እንያችሁ…..እያልኩ ነው፡፡ እኔን ዲቪ ይርሳኝ…ዘውዱ አዲስ በዲቪ አሜሪካን ሲከትም ጊዜ ዘነጋሁት…ዱላችንን ይዘን ከቤት ቤት እየዞርን እንጨፍራለን፡፡

     ሀይሌ ሩት‹‹..እርጅና ጣና ድቅን አለ ፊቴ…›› እንዳለው ‹‹ጉርምስና መጣና ውፍር አለ ድምጼ..›› ሳልል በፊት ስለነበር ያኔ በጥሩ ድምጽ ጨፈርኩ፡፡ ‹‹..ሆያ ሆዬ…ሆሆሆ..›› ዱላው እግም..እግም…ቆርኪ ቀጥቅጠን በስተን በሽቦ አስረን ያዘጋጀነው እንደ ጽናጽል የሚንሸዋሸው….ክሽክሽም እንደዛው ይንከሻከሻል፡፡ ክፈት በለው በሩን የጌታዬን…ክፈት በለው ተነሳ ያንን አንበሳ…ሰፈራችን ላሉ ጥቂት ጊቢ ያላቸው ቤቶች የሚባል ነው፡፡ ሌላው ልሙጥ በረነዳ የናፈቀው መንደር ስለሆነ ቀጥታ ሄዶ ሆያ ሆዮ በማለት ይጀመራል…..ይጨፈራል፡፡ አሁን ወዳጄ ፋሲል እንዳለውም

"..እዛ ማዶ አንድ ሲሳይ..
እዚ ማዶ ሌላ ሲሳይ..
የእከሌ ልጅ..ሔደ ፈረንሳይ::›› አይነት ቅጥ ያጡ ግጥሞች ዛሬ ሳይሆን መሰግሰግ የጀመሩት በእኛ ጊዜም ነው፡፡
እዛ ማዶ በረኪና…እዚህ ማዶ በረኪና
የኔማ እንትና….ባለ መኪና..እያለ ይወርዳል፡፡ እናቴም ይሄን ጠልታ ይሆናል እንዳንጨፍር የምትከለክለን፡፡ አንድ ቀን ታዲያ ተደብቄ ጨፈርኩ እና የተሰጠንን ሙልሙል ሸጠን ሳንቲሙን ተካፈልን፡፡ ረስቼው ሳንቲሙን ሳልደብቅ ገባሁ፡፡
ተገኘብኝ… 
አቤት የተገረፍኩት.. አቤት ቁንጥጫው…. በርበሬ ታጠንኩኝ፡፡ ከዛ በኋላ ሆያ ሆዬ የሚለውን ስሰማ ያ-ጣር ያ-ዱላ የታጠንኩት በርበሬ ነው ትዝ የሚለኝ፡፡…..በዘፈን ስሰማ እንኳን መሸሽ ነው የሚያምረኝ…….ዛሬ ግን በትዝታ የተቋጠረ ሲጨፍሩ ማየት እንኳን የማልችለው ሆኖብኛል፡፡ አይ ቡሄ እንደዛ አስገርፎኝ እስከዛሬ አለ……