Saturday, November 10, 2012

የጅማ ልጆች ከድር ሰተቴን የምታስታውሱ…


የጅማ ልጆች ከድር ሰተቴን የምታስታውሱ…
                         በግሩም ተ/ሀይማኖት
      ጅማ ብዙ የሚወጉ ወጋ ወጎች አሏት፡፡ ብዕራቸውን ከአፎቱ የመዘዙ የጅማ ልጆች ይህችን ውበታም የፍቅር ከተማ መዳሰስ እና ማስዳሰስ አልቻሉም፡፡ በአንድ ወቅት ስሄድ መሀል ከተማ ላይ ለከተማዋ የውበት እንብርት ሆኖ የተኮፈሰው አዊቱ መናፈሻ መጸዳጃ ሆኖ ነበር፡፡ እህቴና እኔ አፍንጫችንን አፍነን ዞረን አየን፡፡ እንደ እህያ ጋማ አዊቱን ሁለት ቦታ ከፍሎ የሚያልፈው ወንዝ ደም ግባት እና ውበት ሆናት ሳለ ቦታው ማደሪያና መጸዳጃ መሆኑ አሳዛኝ እንደሆነ ጋዜጣዬ ላይ ጻፍኩ፡፡ ጅማ የሚጻፍ ብዙ ነገር አላት፡፡ የግድ ጅማን ከአባ ጂፋር ጋር ማቆራኘት የለብንም፡፡ አባ ጅፍርን ከጅማ ነው ማቆራኘት ቢያስፈልግ እንኳን፡፡

    ምንክንያት አንድ፡- አባ ጅፋር ሳይኖሩ ጅማ ነበርች አሁንም አለች፡፡
    
    ምንክንያት ሁለት፡- የጅማ ማህጸን አባ ጅፋርን ብቻ ሳይሆን ብዙዎችን አብቅሎዋል፡፡

    ምክንያት ሶስት፡- ዙሪያ ተፈጥዋን ስንቃኝ.. ቦዬ ራሱን የቻለ ምስጢር ነው፡፡ አዊቱ እንዲሁ.. ሰርቦ፣ በዳቡና..ሰዎችን እንይ ካልን /ደጃዝማች ይሁኑ ፊት አውራሪ ማዕረጋቸውን ረሳሁት../ አቶ ተካ ኤገኖ፣ ጋሽ ደርጉ…ከድር ሰተቴ..ብዙ የሚዳሰስ አለ፡፡ ለዛሬ አንዱን ጀመርኩ፡፡

     መውጫው ይሁን መግቢያው ሲጠፋቸው አንዳንዴ እብድ እየመሰሉ የልባቸውን የሚናገሩበት አጋጣሚ ሞልቷል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ከድር ሰተቴ ነው፡፡ ከድር የአባቱ ስም አይደለም ሰተቴ ‹‹ሰተተተትትትትት…›› እያለ የሴቶችን እንትን ሳያስቡት መንካት ይወዳል፡፡ እብድ ለመምሰል ብሎ ብቻ ሳይሆን ሳስበው እዛ ስር የተለከፈም ይመስለኛል፡፡ ቀርከሀ ዱላ ይይዛል፡፡ ጆኒዎከርም ይሉታል፡፡ እብድ መስሎ እብድ ያልሆነ ሁሌም ጽዱ ሆኖ የሚታይ፡፡ በሰከንዶች ውስጥ ግጥም እየገጠመ አጥረግርጎ ሚሳደብ ሲያሻው የሚያሞግስ፡፡ ለነገሩ አሞግሶ የሚያውቀው ኢህአፓን ብቻ ነው፡፡ በኢህአፓ የመጣበትን አይቀበልም፡፡ ቀንደኛ የኢህአፓ አባልና ታጋይ ነበር ሲባል ሰምተናል፡፡ ግን አላየንም፡፡ በ1977 ዓ.ም ወሎ ብድርቅ ተጠቅቶ ሰው በርሃብ እያለቀ አስረኛው የአብዬት በዓል ይከበር ነበር፡፡ ኢሠፓአኮም ወደ ኢሠፓ ይሸጋገር ነበር፡፡ ይሄ ጉዞ እድገት ይሁን ውድቀት ብዙ ፖለቲከኞች ግራ ሲጋቡበት እንጂ ሲተነትኑት አይስተዋልም፡፡ ምስጢሩን ጓድ መንግስቱ ብቻ ሳይሆኑ አልቀሩም የሚያውቁት፡፡ የሆነው ሆኖ ኢሠፓአኮ የሚለውን ‹‹ኢሳያስ ሰናይትን ፓንቷን አስወልቆ ኮሞኮማት›› ሲሉ በሰዓቱ ወጣቶቹ ያላግጡበት እንደነበር ትዝታ መጨለፍ እንችላለን፡፡

      ከድር ሰተቴ የሰባሰባቱን 10ኛ የአብዮት በዓል በተጋነነ ወጪ መከበር ከርሃቡ ጋር ሲገልጸው ‹‹ሰባሰባት አንድ እንጀራ ለሰባት…ሰባሰባት..አንድ እንጅራ ለሰባት….ኢሠፓኮ ባዶ ፓኮ›› ይል ነበር፡፡ በአንድ ወቅት የቀበሌ ፕሬዘዳንቶች…የመከላከያ ሚኒስትሮች… ማለቴ የቀበሌ ሊቀመንበሮች አብዮት ጠባቂዎች ራሳቸውን እንደ ፕሬዘዳንት እና መከላከያ ሚኒስቴር ስለሚመለከቱ በፍላጎታቸው ልጥራቸው ብዬ ነው፡፡ እዛችው ጅማችን ውስጥ ተሰብስበው አለም ደርግ ብለው ይጠጣሉ፡፡  ባዶ እጁን ሆኖ ሽጉጥ እንደያዘ በሽጎጥ ቅርጽ እጁን አድርጎ ‹‹እንዳትበላሽ እጅ ወደላይ..›› ይላል፡፡ ግማሾቹ ስተው ሁሉ ነበር አሉ፡፡ ቤቱን የፈነዳ ሽንት ቤት አስመስለውት፡፡ ተደናብረው የብርጭቆ መዓት የከሰከሱትን ቤት ይቁጠራቸው፡፡ ወይ ልባቸው!!! ከድር ሰተቴ ተያዘና ታሰረ፡፡ ‹‹እኛ ያልነው ለፉገራ እናንተ አደረጋችሁት የመግደል ሙከራ..›› ብሎዋቸው ነበር ይባላል፡፡  ስለከድር ሰተቴ ብዙ ማለት እችላለሁ፡፡ እስኪ እናንተ የምታስታውሱት ምን ያህሉን ነው?
   
       ስለ ጅማ እመለሳለሁ አዊቱ ሻይ እየጠጣችሁ ጠብቁኝ

ስደት እና ፍቅር
በግሩም ተ/ሀይማኖት
ርዕሴን ሲያዩ ምን አገናኝቶት ስደትን ከፍቅር ጋር ለጠፈው እንዳይሉ፡፡ እመነኝ..እመኝኝ ግጥም አድረጎ ይገናኛል፡፡ ካላመንከኝ እንወራረድ ብዬ እንዳልሞግትህ ፍቅርን እንደ ፊልም የሚያሳይ ስክሪን የለኝም፡፡ መሞከሪያ ቴስት ላይትም አልተሰራለት…ወደፊት ከተሰራ አብረን እናያለን፡፡

የሰዎችን የፍቅር ታሪክ እንደመስማት የሚያስደስት ነገር አለ? ታዲያ ዝም ብሎ ፍቅር ብለው በየቤርጎው በየእንትኑ ስር የሚፈጽሙትን የአንቀህ ጣለኝ ድራማ አይደለም፡፡ የእውነተኛውን ፍቅር ታሪክ መስማት ያስደስተኛል፡፡ የእናንተን እንጃ ግን ባትውዱ ሁሉ ስለፍቅር የሚያወሩ እነዛን ሁሉ ጋዜጦች ተሸምታችሁ

ትገዙ ነበር፡፡ ለነገሩ አስትሮሎጂ የሚል ጥንቆላም አላቸው እሱንም ፈልጋችሁ ይሆናል፡፡ ስለ ፍቅር ማንበብ መስማት ቢያስደስትስ ምን ያሳፍራል? የሰውን ፍቅር የማይወድ ሴጣን ብቻ ነው፡፡

ስለምወድም የብዙዎችን የፍቅር ታሪክን ከሰማሁ በኋላ ነው ስደትና ፍቅር ብዬ የተነሳሁት፡፡ ውይ የኔ ነገር ተነሳሁ እንዴ? አረ!! አልተነሳሁም፡፡ ብዕሬን ያነሳሁት ለማለት ነው፡፡ ለካ ብዕርም አላነሳሁም ቀጥታ ሀሳቤን ወደ ኮምፒዩተር የተየብኩት በሚል ይቀየርልኝ፡፡ እንዲያውም አንዳንዴ ሳስብ ፍቅር ይሰደዳል አይሰደድም? የሚል መጠይቅ ቢቀርብ ስንት አይነት መልስ ይሰማል? ይሰደዳልም በሉ አይሰደድም ለጊዜው አቆዩኝ እና ‹‹ስደት ላይ ፍቅር ይከሰታል አይከሰትም?›› በሚል ርዕስ ውይይት ከሰዎች ጋር አነሳለሁ፡፡ ያላቸውን ሀሳብ ለማወቅ ግዴታ ተቃራኒ ሆኜ መቅረብ ይጠበቅብኛል፡፡ ‹‹ስደት ላይ ፍቅር አይከሰትም..›› ብዬ የውሸቴን ሽንጤን ገትሬ እከራከራለሁ፡፡ እንዲያው ለአባባል ሽንጤን ገትሬ አልኩ እንጂ እንኳን ልገትረው ለራሱ መኖር እና አለመኖሩን አይቼ አላውቅም፡፡ የት ጋር ይሆን ያለው? አሳዩኝ ምሩኝ መንገዱን…የሚለውን ዜማ ማቀንቀን ይጠበቅብኛል መሰለኝ ቦታውን ለማዎቅ፡፡ ለነገሩ ሽንጥ ያለው ስጋ ቤት ነው፡፡ እናላችሁ ስለፍቅር እናውራ….

ስከራከር አዎ! ካልኳቸው በዛው ተስማምተን እንዳንቀር እሰጋለሁ፡፡ ስለዚሀ ተቃራኒ እሆንና ተናደው የሚሰማቸውን እንዲያወሩ አደርጋለሁ፡፡ ይከሰታል ባይ መሆኔ ዝም ብሎ ሳይሆን እኔ ለራሴ ቤተ-ሙከራ ራሴ ነኝ፡፡ የሰው ልጅ ባለበት ሁሉ ፍቅር አለ ባይ ነኝ፡፡ ግን የትኛው የፍቅር አይነት የሚለው ነው መሰረታዊ ጥያቄ፡፡ ሰም ለበስ ፍቅር መስሎ የሸመቀውን፣ ፍቅር የሚለውን ታፔላ ለጥፎ ለጥቅም ሸምቆ የሚገኘውን አይደለም፡፡ ጥቅምን ታርጌት ያደረገውን የውሸት ፍቅር ፍጽሞ ከግምት አንከተውም፡፡ የምንነጋገረው ስለ እውነተኛው ፍቅር ነውና፡፡ እውነተኛው ፍቅርስ ቢሆን በስንት ይከፈላል? አንዳንዶች እንደ ሸንኮራ አገዳ ሰነጣጥቀው ሸንሽነው ሸንሽነው ያበዙታል፡፡ ለእኔ ግን ፍራንሲስ ቦምና ‹‹ፍቅር ውሻን እንኳን በዜማ እንዲያላዝን ያደርገዋል..›› እንዳለው ሀያል እና አንድ ብቻ መሆኑን ነው የሚገባኝ፡፡ አብሮኝም የተሰደደው እውነተኛው ፍቅር ነበር፡፡እንዲያውም አድንቄዋለሁ አብሮኝ በመውጣቱ…ብዕርም አስነስቶኛል፡፡
‹‹..ስደት ከሄድኩበት ነጻነት ፍለጋ
ፍቅርሽን ይዤ ከትዝታ ስዋጋ
ሀይል የለኝ ጉልበት
ታግዬ የማሸንፍበት…›› አስብሎኛል፡፡ በሰፊው ከከተብኩት ቦጨቅ ደረኩት ነው፡፡
አፈር ነህና ወደ አፈር ትመለሳለህ የሚለው ቃል ተግባራዊ ሆኖ አፈር እስካልተጫነው…አፈር ረገጠ ድንጋይ፣ ጎጆ ቀለሰ፣ ፎቆ ቆለለ ጎዳና አደረ፣ ስደት ወጣ እስር ቤት ገባ…ቦታና ጊዜ ሳይመርጥ አጅሬ ፍቅር ቂብ ይልበታል፡፡ ሌላው ቀርቶ ወዳጄ ሙት ለካ ሆድህ ባዶ ሆኖም ፍቅር አለ፡፡ ስደት ላይ ያገኘሁት ዋሲሁን…ውይ የኔ ነገር ጋሼ ዋሲሁን ማለት ነበረብኝ የሀያ አንድ አመት ልጅ አለችው እኮ!..ለነገሩ ራሱ ተመለጠ እንጂ አንድ ፍሬ ቦርቆ ያልጠገበ የሀምሳ ሰባት አመት ጎልማሳ ነው፡፡

ስማኝማ ዋሲሁን መቼም እኛ ‹‹ከአሜሪካና ከሞት የሚቀር የለም ካልን ሰነበትን ዛሬ አሜሪካ ሆነህ ነው የምታነበኝ እና የማታፍር ከሆነ የወሎ የፍቅር ታሪክህን ላስፍራት? አጭ!...ምን ሆንክ ግሩሜ ወደ ታሪክህ ተመለስ ያንተን ዋሲሁን እኛ የት እናውቅልሀለን….ብዬ ራሴን ተቆጣሁትና ተመለስኩ፡፡ ሆድ እርቦት የፍቅር ርሃብም ተደርቦ እንደሚያስቃይ የነገረኝ ዋሲሁንን ገጠመኝ እንመልከት፡፡ ‹‹በ1977 ወሎ በርሃብ ተጠቅቶ ነው፡፡ የሚላስ የሚቀመስ ታጥቶ ርሀብ ሲያሳድደን እኔን ግን እህል ብቻ ሳይሆን ፍቅርም እየራበኝ እሰቃይ ነበር፡፡ ወደ አሰብ ለመሄድ የተነሱ ቤተሰቦች በአካባቢያችን ሲያቋርጡ አይኔን ብቻ ሳይሆን በርሃብ የተጣበቀ አንጀቴን ጭምር አጠገበችው፡፡ በልቶ ሳይሆን እሷን አይቶ…እነሱ ሁለት ቀን አድረው ጎዞዋቸውን ቀጠሉ፡፡ ርሃብ ካደቀቀው እኔነቴ ላይ ልቤን መንትፋ ነጎደች፡፡ ታዲያ ያችው እምንቃመሳት እህል እንኳን አልበላ አለችኝ፡፡ ርሃቤ ጸሀይ ይመር ሆነች፡፡ ቤተሰቦቼን ይዤ ወደ አዲስ አበባ ልሄድ የነበረውን ሰርዤ እነሱንም ትቼ ወደ አሰብ አቀናሁ፡፡ ይሄው እስካሁንም ከቤተሰቦቼ አልተገናኘሁ፡፡ ታዲያ አላጣኋትም፡፡ የያኔዋ ጸሀይ ይመር የአሁኗ ባለቤቴ ሀያት ይመር ናት አንድ ልጅም ያስታቀፈችኝ እሷ ናት ብሎኛል፡፡ ከፈቀደ እጅግ ደስ የሚል ታሪኩን ሙሉውን አስነብባችኋለሁ፡፡

ለዋሲሁን ፍቅር ይሰደዳል ሳይሆን ፍቅር ያሰድዳል የሚለውም ይሰራል፡፡ ቤተሰቦቹን በዛ ችግር ወቅት አስትቶ አሰብ ያሰደደው ፍቅር ነው፡፡ ለእኔ የሚመስለኝ ሰው እስከተሰደደ ፍቅር የማይሰደድበት ምንም ምክንያት የለውም፡፡ ፍቅር ይሰደዳል የሚለውን ለማጠናከር ብዙ መዳከር የለብንም ብዙዎች ስንሰደድ ፍቅረኛ አልነበረንም? ከነበረንስ ፍቅራችንን እንደልብስ አውልቀን ጥለነው ወጣን? እኔ የራሴን የማስታውሰው የውዴን ፍቅር ሰንቄ ነበር ስደትን የተጋተርኩት፡፡ ስለዚህ ፍቅር ይሰደዳል፣ ፍቅር ያሰድዳል፣ ፍቅር ስደት ላይ ይከሰታል እላለሁ፡፡ እናንተስ? ለጊዜው በዚህ እንወያይ
በቀጣይ እመለሳለሁ፡፡

Monday, November 5, 2012

የምትናደጅ ከሆነ ይህንን እውነታ አታንብቢ


የምትናደጅ ከሆነ ይህንን እውነታ አታንብቢ
‹‹ብልቶቻችሁን የአመጻ ጦር እቃ አታድርጉ..››  
                             ሐዋርያው ቅ/ ጳውሎስ
     በግሩም ተ/ሀይማኖት

      ይሄን ግን ባታነቡት ይሻላል ምንም የማይረባ ነገር ልንገርህ /ልንገርሽ/ ብዬ ባለፈው የጻፍኩ ጊዜ ‹‹እሰይ!!..ወንዶቹን ነገርክልን›› ያላችሁ የሄዋን ልጆች ዛሬ ተረኛ ናችሁ እና ስለእናንተ እናውራ፡፡


   በሴቶች ላይ የሚደርስን በደል፣ ሴትነት የሚያመጣውን ጣጣ፣ ያላቸውን ችግር አስመልክታ ‹‹ማንን ልርገም?›› በሚል ርዕስ እዚሁ ፌዝቡክ ላይ ተከታታይ ፅሁፍ የምታቀርብ ጸሀይ በየነ የተባለች ጓደኛዬ አለች፡፡ ማንን ልርገም ያለችው ሴቶች ላይ ከሚደርሰው ሳንካ አንጻር ማህበረሰቡን፣ ባህሉን፣ ስንኩል አስተሳሰባችንን ወይስ ሴትንቴን /ሴት መሆኔን/…ለማለት ፈልጋ እንደሆነ እግረ መንገዴን ተንፍሼ ልለፍ፡፡ ታዲያ ሴቶቹም የሚያደርሱትን ጥቃት ግምት ውስጥ ከታ ሚዛናዊ መሆን እንዳለባት አስብ ነበር፡፡ ግን አልጠቆምኳትም፡፡ ያውስ ሴቶቹ የሚያደርሱት ጥቃት ከላይ እስከ ታች የህይወትን ምህዋር ያናጋ የለ?  

   ሴት መሆን ጸጋ ነው፡፡ ካወቅሽበት ሴትነትሽን ካከበርሽውና ካስከበርሳው ጌጥ ነው፡፡ ወንዶች የማያገኙትን የእናትነት ፀጋ ተላብሰሻል፡፡ ካላከበርሽው እና ካላስከበርሽው ግን ብትወልጅ እንኳን የእናት ቅሌታም ትሆኝና ለልጅሽ ማፈሪያነትሽ ይጎላል፡፡ ልብ በይ የሄዋን ልጅ ሆይ ሔዋን ስሜቷ በነዳት ሮጣ ቃል ስታ ሞት ብታመጣ ለልጆቿ ሁሉ /ለሴቶች/ መወቀሻ ሆናለች፡፡ አንቺስ ለልጆችሽ መወቀሻ መሆን ትፍልጊያለሽ? በሌላ በኩል ደግሞ ልብ ልትይ የሚገባሽ በሔዋን የመጣውን ሞት ለማጥፋት መድኃኒቱም የተገኘው ከሴት መሆኑን አትርሺ፡፡ ከድንግል ማርያም ማህጸን የተገኘው ከስጋዋ ስጋ ከደሟ ደም የተጋራው ነው ያዳነሽ፡፡

     ስለዚህ ተፈለኩኝ ብለሽ ሴትነትሽን ከመነዘርሽው፣ በየሱሪው ላይ ከከደንሽው ሄዋን ስሜቷ በነዳት ሮጣ ቃል ስታ በእጸበለስ ያመጣችውን ሞት ከዝሙት አልጋሽ አፍሰሽ ሞትን ለየሰዉ የምታድይ በሴጣን ግዛት ያለች ሔዋን ትሆኛለሽ፡፡ እውነት እውነት እልሻለሁ ሴትነትሽን ካከበርሽው አንቺም የተባረክሽ ነሽ፡፡ መድኃኒት የሆነ ባትወልጂም ፍቅርን የሚሰብክ በፍቅር ያደገ ልጅ ይኖርሻል፡፡ ልጅ ባይኖርሽ እንኳን ቢያንስ በጸጸት ያላደፈ ንጹህ ህሊና ይዘሽ ትኖሪያለሽ፡፡  

   በተለይ ያለ እድሜሽ ወጣት ልሁን ብለሽ ባውንድ እየመዘዝሽ ልጅሽን ልጅሽን የሚያካክሉ ጎረምሳዎች ጠረን ከናፈቀሽ፣ ተጋድመሽ ልታጋድሚቸው ካሰብሽ..ኑሮሽን ናድሽ፡፡ መቼም አጋድሜ የእናትነት ምክር ልለግሳቸው ነው አትይንም፡፡ አንድ ቀን ትጋለጭና ቤትሽን ስትንጂ፣ ልጆችሽን ስትበትኝ ፀፀት ሸንቁጦ..ሸንቁጦ ያርመጠምጥሻል፡፡ እድለኛ ካልሆንሽ ጨርቅሽን ጥለሽ..ባትጥይ እንኳን ከእብድ ሳትሻይ ትኖሪያለሽ፡፡

   እውነት እንነጋገር ከተባለ ትዳር ላይ ያለ ሰው በሶስት ምክንያት ነው አይኑን ወደ ውጭ የሚልከው፡፡

   አንድ፡- የጎደለ ነገር ካለ ፍለጋ..በተለይ አንቺ ግለሽ እሱ ከበረደ፡፡ አለያም ከአቅሜ በላይ ነው የሚለውን ካስታወሰሽ….እውነቱ ካልተዋጠልሽ ዞር ብለሽ የልዕልት ዲያናን ታሪክ ተመልከች፡፡ ልዕልትነቱን ጠልታ ይመስልሻል ወደታች ወርዳ ከሰራተኛዋ ጋር የተንጎዳጎደችው? ከንጉስ ቻርልስ ያጣችውን እርካታ ፍለጋ ስትማስን የተልሞሰሞሰውን ንጉስ የሚያስንቅ ተገኝቶ ለመሆኑ ፍቺ ስትጠይቅ ያለችውን አስቢ፡፡ ከንጉሱ ያላገኘችውን በስርቆት ህብረ-አንሶላ ሜዳዋ አፍሳለች፡፡ ታዲያ መስረቅሽም ሆነ መሰረቅሽ በጎ ነው በርቺ እያልኩሽ እንዳይመስልሽ፡፡ ሌብነትን የሚያበረታታ ቲፎዞ አልሆንም፡፡ ወደ ውጭ ከሚያስኬዱ አንዱ ችግር ይሄ ነው እያልኩሽ ነው፡፡ ታዲያ በስርቆት መንጎዳጎዱ ሳይሆን በግልጽ መነጋገሩ…ብሎም ችግሩ ካልተፈታ ወደ ስነ-አዕምሮ ጠበብት ብቅ ማለት ነው መፍትሔው ልልሽ ነው፡፡

ሁለት፡- እሾክን በእሾክ ብለሽ የእሱን እየተሰረቁ መንጎዳጎድ ለመርሳት ወይም ብድር በምድር ብለሽ እሱ በፊት በር ሲወጣ አንቺ በጓሮ ከወጣሽ ነገር አበላሸሽ፡፡ ማን እሳትን በእሳት ሲያጠፋ አየሽ? እሳትን በውሀ እንጂ…እሱ እሽኮለሌ ሊል ሲወጣ በ ‹‹እህህ..ታ›› ተሰንገሽ ተርመጥመጭ እያልኩሽ አለመሆኑን ተረጂኝ፡፡ ምን ቆርጦኝ እላለሁ፡፡ ኑሮን የመምራትም ሆነ የመናድ ብርታት እና ብልሀት ያለው ሴት እጅ ነውና መክረሽም አስመክረሽም መልሺው፡፡ ምን አጎደልኩ በይው፡፡ ሌላውን ዘዴ አንቺው ፈብርኪው አመሉን ታውቂ የለ?

ሶስተኛ፡- ከሁለቱ ውጭ በሆነ መንገድ አይንሽን ከወረወርሽ፣ እግርሽን ካበደርሽ፣ አፍሽን ካስከደንሽ፣ ጡትሽን ካስዳበስሽ..የዘማዊነት አመል አለብሽ፡፡ የዘማዊነት አመል ካለብሽና የምትናደጂ ከሆነ ይህን አታንብቢ፡፡ የሌለብሽ ደም ብዛት ከላይ ታች እንዳይንጥሽ፣ ጨጓራሽን ፈቅፍቆ…በተወደደ ስኳር ስኳር እንዳይጨምርብሽ፡፡ የምናገረው ግን የእውነቶች እውነት ነው፡፡ ካልፈለግሽ አለመቀበል መብትሽ ነው፡፡ እኔ ግን መደባበቅ ይብቃ ብያለሁ፡፡    

  ፓውደርና ቀለም አድምቆሽ ልጅ የሆንሽ ሲመስልሽ፣ ስሜቱ በነዳው የሚነዳ ወንድ በአይኑ ሲሸኝሽ..ባየው በር ልግባ የሚል ስሜተ ውሻ ሲጎነታትልሽ ሹገር ማሚነት ካማረሽ ስሜትና ቅሌት ቆመው እየጠበቁሽ ነው፡፡ የእድሜሽ ጠቋሚ ቀስት ግን ልጆችሽን ድረሽ የልጅ ልጅ ማቀፊያሽ ነው የሚለው ላይ እያመለከት ይሆናል፡፡ ይህን ሰል ግን ካልወለድሽ፣ ወጣት ከሆንሽ እንደፈለገሽ ሁኚ ለማለት አይደለም፡፡ ሴትነትሽን እንድታከብሪው ነግሬሻለሁ፡፡ የልጆችሽን ፍቅረኛ በባውንድ እየገዛሽ ስትሻሚ በለገስሽው ፍራንካ ልጅሽን የሚያባልግበት መሆኑን ብታውቂ ምን ይሰማሻል? መቼም እሰይ ስለቴ ሰመረ ብለሽ አትዘምሪም፡፡ ለንሰሀ ፊትሽን ወደ እግዚአብሄር ቤት ማዞሪያው ሰዓት ላይ ቆመሽ ባሌ ሄደ፣አላየኝም..እርካታን ከፍንዳታ ፍለጋ ስትሮጪ ‹‹ሰዶምና ገሞራ በእኛ ቤት›› የሚል ድራማ ለመስራት አታስቢ፡፡ በተለይ ልጆችሽ አግቡ የሚለው እድሜ ላይ ከሆኑ እየተሸማሻቸው መሆኑን ነጋሪ ያስፈልግሽ ይሆን? ለነብስሽ ቤተክርስቲያን ሄደሽ መቋሚያ ለስሜትሽ ጎረምሳ የምትመረኮዢ ከሆነ እህቴ ሙች አትድኝም፡፡ ዘማዊዋ ሴት በእንባ እግር አጥባ ተፈወሰች እንጂ በዝሙቷ አልተሸለመችም እኮ!!..ስለዚህ ለልጆችሽም የሀጢያትሽን ውርስ ከምታወርሺ ፍቅርሽን ይራባሉና ስጫቸው፡፡ እርፍ ብለሽ ብትቀመጪ አትገነፍይ፣ አናትሽ ላይ ወጥቶ አያቀውስሽ..ይልቅ መጥፎ ስራሽ ነው ጊዜ ጠብቆ የሚያሳብድሽ፡፡

    አበው ‹‹..ጎሽ ለልጇ ስትል..›› የሚሉትን አስቢ፡፡ ባልሽ ጭንቅላቱ ደንዞ ካስማውን ወድሮ ለተከላ ሲቅበዠበዥ በጭኑ ካሰበ ለልጆችሽ የቀረሽው አንችነሽ፡፡ ለመኖር ምግብ፣ ለነፍስ ጸሎት፣ ለበሽተኛ መድሀኒት..ጉሉኮስና ኦክስጂን..የሚያሰፈልገውን ያህል ልጆችሽም ሙሉ ሰው ለመሆን ከታደሉ የሁለታችሁም ካልሆነ ያንቺ ፍቅር እንደሚያስፈልጋቸው ለሰከንድ አትርሺው፡፡ አይ እንደ ቦይ ውሀ ላፈሰሰኝ ሁሉ እፈሳለሁ፤ ለነካኝ ሁሉ እወድቃለሁ ብለሽ ሙዳየ እንቁሽን የትም የወደቀ ቅል ካረግሽው ምነው ካንቺ ባልተወለዱ፡፡ ፍቅር የተራቡ፣ የፍቅር ድርቅ ያጠቃቸው፣ ቤተሰብ የናፈቁ ልጆች ታፈሪያለሽ፡፡ እነካናዳ፣ እነአሜሪካም ቢሆን ለምግብ ርሃባችን ስንዴ ይሰጣሉ እንጂ ለቤተሰብ ፍቅር ርሃባችን የሚረዱን የላቸውም፡፡ ያለው አንቺ እጅ ነዋ!!!!

   ወጣቷም ሆንሽ ትልቋ፣ ጎረምሳውም ሆንክ አባት ፍንዳታ ቅዱስ ቃሉ ‹‹ብልቶቻችሁን የአመጻ ጦር እቃ አታድርጉ..›› ማለቱን አስታውሱ፡፡

  ስሜተ አፍላዋ እህቴ ብር ብለሽ አትብረሪ..አልጋ ይዘሽ እንዳትቀሪ፡፡ እናቴ ዘመኑ ከፍቷል ከመክፋም ከርፍቷል፡፡ ጤነኛና ጤና ያጣው ተማቷል፡፡ ህይወትሽ ስስ ናት፡፡ አንዴ ካጋደለች ለመመለስ ትከፋለች፡፡ ያውም ፍሬ ማፍሪያሽ ውስን ናት፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ስደት ላለሽው እህቴ አንድ ገጠመኜን ላውጋሽ እና ልሰናበት፡፡ አንቺ ግን እወቂበት ትምህርት ነው፡፡

      የመን እንደመጣሁ አዲስ አበባ የማወቀው አብርሀም የሚባል ልጅ ጋር ሄድኩኝ፡፡ ሚስቱ የውበት ሳሎን ስላላት ቤት በዋለች ቀን የሴት እድር የሚሰበሰብበት አዳራሽ ይመስላል ቤታቸው፡፡ በሄድኩበት ጊዜ ጫወታን ጫዎታ ጠለፈውና አንዷ ስንት አመቴ ይመስልሀል? አለች፡፡ መቼም ሴቶች እድሜ ላይ ችግር ነው፡፡ አንዳንዴ የእናንተ /ሴቶቻችን/ ካላንደር ለብቻ ሁሉ ይመስለኛል፡፡ አንዴ በአንድ ቀን በአንድ ሰዓት አንድ ሰፈር ውስጥ እኩል የተወለድን መሰሉ አስማማው የምትባል ልጅ ለጓደኞቿ 16 አመቴ ነው ብላቸው እኔን ጠየቁኝ ያኔ 22 አመቴ ነበር፡፡ ነገርኳው፡፡ ውሽታም..ውሸታም ሲሏት ‹‹ዋሽታ አይደለም የእነሱ ቤት ካላንደር ቶሎ ቶሎ ስለማይገለጥ የቆጠረችው የተገለጸውን ብቻ ነው›› ብዬ ማለፌን አስታውሳለሁ፡፡

     የማይወዱትን እድሜ ቆጠራ ታዲያ እንዴት እንዲህ አለችኝ አልኩና ብትናደድም ትናደድ ብዬ እውነተኛ ግምቴን 39ወይም 40 አልኳት፡፡ ‹‹..ውይ ለምን ሚኒስከርት አትገዛልኝም፡፡ ህፃን አደረከኝ እኮ 56 አመቴ ነው፡፡›› ከምር ደነገጥኩ፡፡ በእንጆ ስጋ ተሰርታ የማታረጅ ሁሉ ነው የመሰለኝ፡፡
   ‹‹የመን ብቻ 22 አመት ኖሬያለሁ፡፡››
    ‹‹ይህን ያህል አመት ቆይተሸ ምን አፈራሽ እስከዛሬ እንደምሰማው እንደሌሎች ሴቶች ልጅ ብቻ ነው ንብረትም አፍርተሸል?....›› ቤቢ ፊቷን ቋጠረችው፡፡ ‹‹ኡፍፍፍፍፍ…›› ብላ በረጅሙ ስትተነፍስ ከሱናሚ የተረፈ ንፋስ አሰባስባ የተላከብኝ ይመስል ሊያንገዳግደኝ ነበር፡፡
‹‹እስኪ ተወኝ ለእኔ ሳይነጋ ጨልሟል፡፡ ገንዘብ ሳሳድድ ሁሉን ነገር ዘንግቼዋለሁ፡፡ ገንዘቡን አግኝቼ በድን ሆኛለሁ፡፡ አንተ ጋዜጠኛ ነህ ሲሉ ሰምቻለሁ፡፡ ከእኔ ይማሩ ወጣቶቹን ምክራቸው፡፡ በጊዜያቸው ካልተጠቀሙ ህይወታቸው ይበላሻል፡፡ አዲስ አበባም ሰው ቤት ሰርቻለሁ፡፡ እዚህ ከመጣሁ ስሰራ ቤተሰቦቼም ልለውጥ ስል ቦታ ገዛሁ ቤት ሰራሁ..ወጣትነትም ስለነበር ደስ ይላል፡፡ ያኔ ፈላጊው ብዙ ነው፡፡ ስትወጣ ስትገባ…ደስ ካለህ ጋር ትዝናናለህ፣ ትገባበዛለህ፡፡ ((ትዝናናለህ፣ ትገባበዛለህ የሚለው በጨዋኛ አባባል ነው፡፡ ታዲያ ሲመነዘር መዝናኛው፣ መገባበዣ አልጋ ነው ልትል ፍልጋ ነው አላልኩም፡፡ ግን የፍቅር ጠረን እንዳለው ለማሳየት ነው ድርብ ቅንፍ ያደረኩት፡፡))   
 ..ከስንት ጥረት በኋላ የምፈልገውን አሟልቼ ወልዶ ማሳምን ስናፍቅ ለካ ረፍዶብኝ ነበር፡፡ ሁሉም በወቅቱ ካልሆነ…አለችኝ፡፡ ለምን ይመስልሻል ይህን ያነሳሁት እታልሜ ወቅትሽን እወቂ ለማለት ነው፡፡
                 ጨረስኩ አስተውሎ መራመድ ብልህነት ነው፡፡