አሸንድዬ በዓል በላሊበላ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አማኞች ዘንድ የጾመ ፍልሰታ ለማርያምን ፍጻሜ ተከትሎ የሚከበረው የአሸንድዬ በዓል በዋናነት በሰሜን ኢትዮጵያ ከሚከበሩ መንፈሳዊ በዓላት መካከል የሚጠቀስ ነው፡፡
በትግራይ፣
ዋግና ላስታ ከሚከናወኑ በርካታ ሃይማኖታዊ ባህላዊ ጨዋታዎች መካከል እንደ እሽውላሌ፣ ጊጤ፣ ገና ጨዋታ፣
አሸንድዬ፣ ሙሻሙሾ እና ሆያ ሆዬ የመሳሰሉት በዓላትም በዐበይትነት ይጠቀሳሉ፡፡ በነሐሴ ወር አጋማሽ ከቅድስት
ድንግል ማርያም በዐለ ዕርገት/ፍልሰታ/ ጾም ፍች ጋራ ተያይዞ የሚከበረው የአሸንድዬ በዓል ማራኪና ልዩ ባህላዊ
ጨዋታ ነው፡፡
በቀድሞዋ
ሮሃ በኋላ ላሊበላ የሚከበረው በዓሉ፣ በላስታ “አሸንድዬ”፣ በትግራይ “አሸንዳ”፣ በዋግ “ሻደይ”፣ በራያ ቆቦ
“ስለል በይ” በመባል ተቀራራቢነት ባላቸው ስያሜዎች ይጠራል፡፡ በሁሉም አካባቢዎች በተመሳሳይ ወቅት ልጃገረዶች
ከወገባቸው ላይ ሣር መሰል ቅጠል በማሰር ከቤት ቤት በመዘዋወር የተለያዩ ጣዕመ ዜማዎችን በማሰማት የሚጫወቱት
ጥንታዊ፣ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ጨዋታ ነው፡፡ ዘንድሮም ከላሊበላ በተጨማሪ በላስታ እና በመቐለ በደማቅ ኹኔታ
ይከበራል፡፡
በትግራይና
በአማራ ክልል የሚከበረው ይኸው በዓል በተለይ በዚህ ዓመት በላሊበላ በታላቅ ድምቀት እንደሚከበር ታውቋል፡፡
የቅዱስ ላሊበላ ደብርን ጨምሮ የወረዳ ቤተ ክህነቱን በበላይነት በሚመራው የቅዱስ ላሊበላ ደብር አስተዳደር ካህናት
የሚሳተፉበት ያሬዳዊ ዝማሬና ቅኔ የበዓል ዝግጅቱ አካል ሲኾን የበዓሉ መክፈቻ ሥነ ሥርዐት በሚካሄድበት ነሐሴ 16
ቀን 2005 ዓ.ም. ሽት የላስታ ላልይበላ ሕዝባዊ ባህል የኾነው የአሸንድዬ ልዩ ልዩ ባህላዊ ጨዋታዎችም
ይቀርቡበታል፡፡
በዓሉን
መሠረት ያደረጉ ጥናታዊ ጽሑፎች በባለሞያዎች ቀርበው የፓናል ውይይት እንደሚካሄድ ለበዓሉ አከባበር ከወጣው መርሐ
ግብር ለመረዳት ተችሏል፡፡ ከነሐሴ 15-17 ቀን 2005 ዓ.ም. በሚቆየው ክብረ በዓል ከክልልና ከፌዴራል መንግሥት
የተወጣጡ ከፍተኛ ባለሥልጣናትን ጨምሮ 200 ያህል ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እንደሚገኙበት ተዘግቧል፡፡
በዓሉ
ባህላዊና መንፈሳዊ ይዘቱን ጠብቆ ተጨማሪ የቱሪስት መስሕብ እንዲኾንና የባህል ገጽታ ግንባታን ወደ ላቀ ደረጃ
ለማድረስ በከተማው አስተዳደርና በክልሉ መንግሥት ትኩረት መሰጠቱ በክልሉ የቱሪስቶችን ቁጥር እንደሚያሳድገው ብዙዎች
ይናገራሉ፡፡
በላሊበላና
አካባቢው የቱሪስት ፍሰቱ ከፍተኛ የሚኾነው በታኅሣሥና በጥር ወራት ሲኾን ይህም በአብያተ መቅደሱ (በቋሚ ቅርሱ)
የሚከበሩ በዓላትን ማእከል ያደረገ ነው፡፡ ባህላዊና ሃይማኖታዊ ቅርስ የኾነው የአሸንድዬ በዓል በአግባቡ ታቅዶና
ተደራጅቶ ለቱሪስቶች ቢተዋወቅ ደግሞ በነሐሴና በመስከረም ወር የቱሪስት ፍሰቱን በመጨመርና የጎብኚዎችን ቀልብ
በመሳብ የቱሪስቶችን ቆይታ ያራዝማል፡፡ ይህም እንደ ቻይና የውኃ በዓል፣ እንደ ስፔን የኮርማ ውጊያ፣ እንደ
ብራዚልና አርጀንቲና የጎዳና በዓል ለመልካም ገጽታ ግንባታ ሊውል፣ ኢንቨስትመንትን ሊያስፋፋና የሥራ ዕድል ሊጨምር
ይችላል፡፡
የአሸንድዬ
ባህላዊ ጨዋታ መገለጫ የኾነው አሸንዳ እንደ ቄጤማ ረዥምና እንደ ቅጠል ሰፋ ያለ ነው፡፡ ቁመቱ ከ80 እስከ 90
ሣ.ሜ ይኾናል፡፡ ለምለም ነው፡፡ በወገብ እንደ ሽብሽቦ ኾኖ ይታሰርና ከግጥሙና ከዜማው ጋራ ተዋሕዶ በዳሌያቸው ላይ
ይዞራል፤ ይሽከረከራል፡፡ በተለይ፡-
“እቴ አይዞርም ወገብሽ
ባቄላን ነው ቀለብሽ”
እያለች የበለጠ ወገባቸው እንዲዞር በግጥምና በዜማ አውጭዋ ስታዜም ተቀባዮቹ ደግሞ አባባሉን ለማስተባበል በኃይልና በዘዴ ወገባቸውን ሲያዞሩ ቅጠሉ ርግፍ እያለ ከወገባቸው ጋራ ይሽከረከራል፡፡
“አሸንዳዬ አሸንዳ አበባ
እሽርግፍ እንደወለባ”
ሲሉና
ሲዞሩም አብሮ በኃይል ይዞራል፤ ከወገባቸው ላይ ርግፍ ይልና ዞሮ ተመልሶ ያርፋል፡፡ አሸንድዬ በተለያዩ የሰውነት
አካላት (በአንገት፣ በትክሻ፣ በወገብ፣ በእጅ፣ በእግር ወዘተ) እንቅስቃሴ ይከወናል፡፡
አንዳንድ
ምሁራን አሸንድዬ ገና ቅድመ ልደተ ክርስቶስ ጀምሮ የክረምቱን (ጨለማው፣ ጭቃው፣ ጎርፉ፣ ዶፉ፣ ብርዱ) መውጣትና
የበጋውን (ብርሃኑ፣ ፀሐዩ፣ የወንዙ ጥራት፣ የአዝርዕቱ ማሸት፣ የአበባው ማበብ) መግባት ምክንያት በማድረግ ደናግል
(አዋልድ) ቅድመ ዕንቊጣጣሽ ሁለት ሳምንት ሲቀረው ጀምሮ አዲሱን ዘመን በደስታና በሐሤት ለመቀበል በብሩህ ተስፋ
ውስጥ ኾነው ይጫወቱት እንደነበር ይናገራሉ፡፡
1 Comments:
Las Vegas Slots 2021 | Casino, Table Games and Table Games
Slots is a 동해 출장마사지 real Vegas 포천 출장마사지 casino slot game. With over 3,000 of the latest slot games, 오산 출장마사지 you are sure to find the right game for you. Play for free 김제 출장마사지 at the 김해 출장마사지 best
Post a Comment
Subscribe to Post Comments [Atom]
<< Home